እድሜን ማዕከል ያደረገ የክብደት ማንሳት ስፖርት ቶሎ የመሞት እድልን በ46 በመቶ ይቀንሳል

እድሜን ማዕከል ባደረገ መልኩ ክብደት በማንሳት የሚሰሩ የሰውነት ግንባታ ስፖርቶች ቶሎ የመሞት እድልን በ46 በመቶ እንደሚቀንስ ተነግሯል።

በአሜሪካዋ ፔንሲልቫኒያ ፔን ስቴት ኮሌጅ ኦፍ ሜዲስን የተሰራ ጥናት እንደሚያመለክተው፥ በክብደት አማካኝነት የሚሰሩ ሰውነትን የሚያጠነክሩ እና የሚያጎለብቱ ስፖርቶች የሞት ተጋላጭነትን በእጅጉ ይቀንሳሉ።

ኮሌጁ ጥናቱን እድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ ባሉ ሰዎች ላይ ያካሄደ ሲሆን፥ የጥናቱ ተካፋዮች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የመስራት ልምዳቸው ምን ይመስላል የሚለውን በጥልቀት መርምሯል።

በተሳታፊዎቹ ላይም ለ15 ዓመታት ክትትል ማድረጉን አስታውቋል።

በዚህም ሰውነትን የሚያጎለብቱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በቀደመ ህይወታቸው ሲሰሩ የነበሩት እና እድሜያቸው ሲያረጅም መስራታቸውን ያላቋረጡ ሰዎች ቶሎ የመሞት እድል በ46 በመቶ ቀንሶ መታየቱን በጥናቱ ላይ ተብራርቷል።

በተለይም ክብደትን በመጠቀም ሰውነትን ለማጠንከር የሚረዱ ስፖርቶችን የሚሰሩ ሰዎች ቶሎ የመሞት እድላቸ አነስተኛ ሆኖ ተገኝቷል የሚለውም በጥናቱ ታል ተቀምጧል።

የጥናት ቡድኑ መሪ ዶክተር ጄኒፈር ካርስችንዌስኪ፥ ሰውነታችንን ለማጎልበት እና ለማጠንከር የምንሰራቸው የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ሁሌም ንቁ እና ራሳችንን እድንችል ያደርገናል ይላሉ።

በተለይም ክብደትን በመጠቀም የምንሰራቸው የሰውነት ማጠንከሪያ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ሰውነታችንን ከማጠንከር በዘለለም ነገሮችን ለመከወን ድፍረት እንዲኖረን እና የመንፈስ እርጋታን ይፈጥርልናልም ብለዋል።

እንዲሁም አጥንታችን ጤነኛ እና ጠንካራ እንዲሆን ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ይላሉ ዶክተር ጄኒፈር።

እነዚህ ነገሮች አንድ ላይ በመደማመርም የሰዎችን ቶሎ የመሞት እድል በእጅጉ እንዲቀንስ አስችለዋል ብለዋል።

ስለዚህ ክብደቶችን በመጠቀም የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የምንሰራ ከሆነ ከማቆም ይልቅ አጠናክረን መቀጠል አለብን የሚል ምክር አዘል መልእክት አስተላልፈዋል።

ከዚህ በፊት ሰርተው የማያውቁ ከሆነ ደግሞ ጊዜው አልረፈደም፤ አሁኑኑ ባለሙያ በማማከር መጀመር እንችላለን ሲሉም ምክራቸውን ለግሰዋል።

እድሜያቸው ከ65 እና ከዚያ በላይ ያሉ ሰዎች ግን ከዚህ ቀደም ክብደትን በመጠቀም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሰርተው የማያውቁ ከሆነ ከመጀመራቸው በፊት የጤና ባለሙያዎችን ማማከር አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል።( ኤፍቢሲ)