አይብን ዘወትር መመገብ ለአጠቃላይ ጤንነት ድርሻው ከፍተኛ መሆኑን አንድ ጥናት አመላከተ።
በኮፐንሀገን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በተደረገው ጥናት አይብ በተለይም የልብ ጤናን ለመጠበቅ ያግዛል ተብሏል።
ተመራማሪዎቹ ለ12 ሳምንታት በዘለቀው ጥናት 139 ወጣቶችን አሳትፈዋል።
ተሳታፊዎቹን በሶስት ምድብ ከከፋፈሉ በኋላም የመጀመሪያውን ቡድን 80 ግራም ከፍተኛ የስብ መጠን ያለው አይብ፤ ሁለተኛውን ቡድን ደግሞ 80 ግራም አነስተኛ የስብ መጠን ያለው አይብ በየቀኑ እንዲመገቡ አድርገዋል።
ሶስተኛው ቡድን ደግሞ ምንም አይነት አይብ አልተመገበም፤ በአንፃሩ 90 ግራም ዳቦ ማጣፈጫ ቀብተው በየቀኑ እንዲመገቡ ተደርጓል።
በዚህም ተመራማሪዎቹ ከፍተኛ የስብ መጠን ያለው አይብ በተመገበው ቡድን ውስጥ የነበሩ ተሳታፊዎች ለሰውነት የማያስፈልገው ኮሊስትሮል፣ የወገብ መጠን እና የደም ግፊታቸው ላይ ምንም ለውጥ አለመታየቱን አረጋግጠዋል።
በአሜሪካ ክሊኒካል ኑትሪሽን ጆርናል ላይ የወጣው የዚህ ጥናት ተሳታፊዎች ለሰውነት የማያስፈልገው ኮሊስትሮል መጠናቸው ምንም ለውጥ አለማሳየቱን የጠቆመ ሲሆን፥
ከፍተኛ የስብ መጠን ያለው አይብ የተመገቡ ተሳታፊዎች ግን ለሰውነት የሚያስፈልገው ኮሌስትሮል መጠን ጨምሯል ይላል።
ከዚህም በተጨማሪ አይብን ከሌሎች ምግቦች ጋር መመገብ የደም ዝውውር እና የምግብ መፈጨትን የተቀላጠፈ ያደርጋልም ነው ያሉት ።
የጃፓን ተመራማሪዎች በቅርቡ ባደረጉት ጥናትም አይብ መመገብ በጉበት ላይ የስብ መከማቸትን እንደሚከላከል አረጋግጠናል ማለታቸው ይታወሳል።
ለመልካም እንቅልፍ፣ ደስተኛ ስሜት እና ክብደት ለመቀነስ አይብ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነውም ተብሏል።( ኤፍቢሲ)