እድሜያቸው ከ75 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ከሚያጋጥሟቸው የልብ ህመሞች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑትን ቀድሞ መከላከል ይችላሉ- ጥናት

የእንግሊዝ የማህበረሰብ ጤና ማህበር በሰራው ጥናት እድሜያቸው ከ75 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ከሚያጋጥሟቸው የልብ ህመሞች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑትን ቀድሞ መከላከል እንደሚቻል አመላከተ።

ሰዎች ሲጋራ አለማጨስ፣ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብን ማስወገድና ያለማቋረጥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ከልብ ህመሞች መከላከል እንደሚችል በጥናቱ ተገልጸዋል።

ማህበሩ እንደሚለው ከ30 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች የልባቸውን እድሜ ለማወቅ ምርመራ ማካሄድ ይገባቸዋል።

በበይነ መረብ የሚካሄደው ምርመራ ልብ በህመም የመጠቃት እድሉ ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ የሚረዳ ሲሆን፤ ድንገተኛ የልብ ህመምን ቀድሞ ለማወቅም ይረዳል።

ምርመራው ህክምና አይደለ፤ የልብ ህመም እንዳለብዎትም አይነግሮትም፤ ነገር ግን ለልብ ህመም ሊያጋልጥዎት የሚችሉ ነገሮችን በመጠቆም እንደ ማንቂያ ደወል ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ተገልጸዋል፡፡

ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ በቂ የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግ እና ከፍተኛ የደም ግፊት ለድንገተኛ የልብ ህመም ሊያጋልጡ የሚችሉ መነሻ ምክንያቶች እንደሆኑም በጥናቱ ተመልክተዋል።

ከሲጋራ በመራቅ፣ ክብደትን በመቆጣጠር፣ ብዙ አሰር (ፋይበር) በመመገብ፣ ቅባት ያላቸው ምግቦችን በመቀነስ፣ በቀን አምስት ጊዜ አትክልትና ፍራፍሬ በመመገብ፣ የጨው ፍጆታ በመቀነስ፣ አሳ በብዛት በመመገብ፣ የአልኮል አወሳሰድን በመቆጣጠር እና የታሸጉ ምግቦችን ባለማዘወተር የልብ ጤና መጠበቅ እንደሚቻልም በጥናቱ ተገልጸዋል፡፡

እስከ አሁን ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የበይነ መረብ ምርመራውን ያካሄዱ ሲሆን፤ ውጤቱ 78 በመቶ የሚሆኑት ተሳታፊዎች ከእድሜያቸው በላይ ልባቸው ማርጀቱን ያሳያል። ይህ ደግሞ ያለ እድሜ ለሚከሰት ሞት ያጋልጣል።

ከእነዚህ ሰዎች መካከል 34 በመቶ የሚሆኑት ከእድሜያቸው አምስት ዓመት የበለጠ የልብ ጤና ሲኖራቸው፤ 14 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ልባቸው ከእድሜያቸው በላይ 10 ዓመት ያረጀ እንደሆነ ተረድተዋል።

በእንግሊዝ ብቻ በየዓመቱ 84 ሺ ሰዎች ከልብ ህመም ጋር በተያያዘ እንደሚሞቱ መረጃዎች ያሳያሉ። (ምንጭ፤ ቢቢሲ)