በከተማዋ መዝናኛ ስፍራዎች በትምባሆ ጭስ ምክንያት አደገኛ የአየር ብክለት እየተከሰተ መሆኑን ጥናት አመለከተ

በአዲስ አበባ ከተማ የምግብና መጠጥ ቤቶች እንዲሁም በመዝናኛ ስፍራዎች በትምባሆ ጭስ ምክንያት አደገኛ የአየር ብክለት እየተከሰተ መሆኑን በመዲናዋ የተደረገ አንድ ጥናት አመለከተ፡፡

በተደረገው ጥናት መሰረት በኢትዮጵያ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ትምባሆ ያጨሳሉ፡፡

በየዓመቱም 17 ሺ የሚሆኑ ዜጎች በትንባሆ ጭስ ምክንያት ህይወታቸው እንደሚያልፍ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በየዓመቱ በሚያወጣው መረጃ መሰረት ለትምባሆ ጭስ የሚጋለጡ እና የሚያጨሱ ሰዎች እንደ የልብ ህመም፣ ስትሮክ የመሳሰሉ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ተጠቂ የሚሆኑበት እድል ከፍተኛ ነው፡፡

የጤና ልማትና ፀረ -ወባ ማህበር አዘጋጅነት በተለይ ትምባሆ ማጨስ በተከለከለባቸው እንደ ሬስቶራንት፣ ባር እና የምሽት መዝናኛ ቦታዎች አካባቢ በትንባሆ ጭስ ምክንያት የሚደርሰው የአየር ብክለት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በአዲስ አበባ በተመረጡ ቦታዎች በተደረገው ጥናት መሰረት ያለው የአየር ብክለት እጅግ አደገኛ በሚባል ሁኔታ ላይ እንደሆነ የጥናቱ አቅራቢ አቶ ደረጄ ሽመልስ  ገልጸዋል፡፡

ከሁለት ዓመታት በፊት ጋትስ ኢትዮጵያ የተባለ ድርጅት በትምባሆ ዙሪያ ባደረገው ጥናት በባሮች እና በምሽት መዝናኛ ክለቦች እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎችና በሬስቶራንት አካባቢዎች ውስጥ የትምባሆ ጭስ ተጋላጮች  ወይም የደባል አጫሾች ቁጥር 60 ነጥብ 4 በመቶ መድረሱን መግለጹ ይታወሳል፡፡

በትምባሆ ማጨስ ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተጠናክረው እንሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ምግብ መድሐኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ በፓርላማ ያፀደቀችው ዓለም አቀፍ የትምባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽን ህጎችን እና ፖሊሲዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል በ2011 ዓ.ም በከተማ ደረጃ ከትምባሆ ጭስ ነፃ የሆነች ከተማ ለማድረግ በእቅድ ይዞ እየተሰራ እንደሆነ ባልስጣኑ አስታውቋል፡፡

የቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፎች እንደሚያሳዩ ህብረተሰቡ በተከለከሉ ቦታዎች ትምባሆ ማጨስ ክልክል እንደሆነ ግንዛቤ አለው ነገር ግን አሁንም ትምባሆ የሚያጨሱ እና የደባል አጫሾች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በመላ አገሪቱ ህዝብ በሚበዛባቸው  አካባቢዎች ትምባሆ እንዳይጨስ የሚደነግገውን አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ ይሰራል ተብሏል፡፡

ከትምባሆ ጭስ ተጋላጭነት በመቀነስ እና በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ እንዲኖር ለማድረግ የመገናኛ ብዙሃን  የማይተካ ሚና እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን ይህንንም አጠናክረው ሊሰሩበት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡