በማህበረሰብ አቀፍ የኤች.አይ.ቪ ተጽእኖ ላይ የተደረገ የዳሰሳ ጥናት ይፋ ተደረገ

በኢትዮጵያ የጸረ ኤች.አይ.ቪ ህክምና አገልግሎት አቅርቦትን በማስፋፋት ጥሩ ውጤት መገኘቱንና በምርመራ አገልግሎቱ ዙሪያ መሻሻል የሚገባቸው ስራዎች እንዳሉ በማህበረሰብ አቀፍ የኤች.አይ.ቪ ተጽእኖ ላይ የተደረገ የዳሰሳ ጥናት አመላክተዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ባሉ ከተሞች የተካሄደው ይህ የማህበረሰብ አቀፍ የኤች.አይ.ቪ ተጽዕኖ ዳሰሳ ጥናት ውጤት እንዲሚያሳየው በከተሞች ዕድሚያቸው ከ15 እስከ 64 ዓመት ከሆኑትና ኤች.አይ.ቪ ካለባቸው ሰዎች ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት አጥጋቢ የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ቅነሳ መጠን እንዳላቸው አሳይቷል፡፡

ይህ የጥናት ውጤት የተባበሩት መንግስታት የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ማስተባባሪያ ፕሮግራም በአውሮፓዊያኑ 2020 ካስቀመጠው በደም ውስጥ የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ መጠን መቀነስ ግብ ከሆነው 73 በመቶ ጋር ተቀራራቢ መሆኑም ተገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 64 ዓመት የሆኑ ኤች.አይ.ቪ በደማቸው ካለባቸው ወንዶች ውስጥ ቫይረሱ እንዳለባቸው የሚያውቁት ከሁለት ሶስተኛ በታች 62 በመቶ መሆናቸውን ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

ይህም ቫይረሱ በደማቸው መኖሩን እንዲያውቁ ለማስቻል ተጨማሪ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

ጥናቱ ከዚህ በተጨማሪም በከተማ የሚኖሩ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 64 ዓመት ያሉት ቫይረሱ በደማቸው እንዳለ የሚያውቁና 99 በመቶ የጸረ ኤች.አይ.ቪ መድሃኒት የሚወስዱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ በከተሞች ከሚኖሩ ኤች.አይ.ቪ በደማቸው ካለባቸው ሰዎች ውስጥ ከአንድ ሶስተኛ በታች ወይም 30 በመቶ የሚሆኑት በደም ውስጥ የቫይረስ መጠናቸው ዝቅተኛ ያልሆኑ ናቸው ተብሏል፡፡ ስለሆነም በደም ውስጥ የቫይረስ መጠንን ዝቅተኛ ለማድረግ በተለይም በወጣት የዕድሜ ክልል በትጋት መስራት እንደሚያስፈልግ ጥናቱ አመላክቷል፡፡

በጥናቱ ይፋዊ ሥነ-ስርዓት የተገኙት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ባለፉት አስራ ሰባት ዓመታት በኤች.አይ.ቪ መከላከልና መቆጣጠር ላይ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመው ቀደም ሲል በየዓመቱ በቫይረሱ ይያዙ ከነበሩት 81 ሺህ ሰዎች አሁን ላይ ወደ 15 ሺህ ዝቅ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔውም ከነበረው 5.8 በመቶ ወደ 0.9 በመቶ ማውረድ የተቻለ ቢሆንም አሁንም ችግሩ አሳሳቢ ስለሆነ ባለፉት ዓመታት በተገኙ ውጤቶች ሳንዘናጋ ልዩ ትኩረት ሰጥተን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሚስተር ሚካኤል ራይኖር ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ፕሮግራምን ለመደገፍ መንግስታቸው ሲሰራ መቆቱን ገልጸው ጥናቱ አሁን ያለውን የኤች.አይ.ቪ ተጽዕኖ ደረጃ ከማሳየት ባለፈ በቀጣይ እንደሀገር በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሊወሰዱ የሚገቡ አቅጣጫዎችን የሚያመላክት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ጥናቱ በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስተባባሪነትና በአሜሪካ ፕሬዝዳንት አስቸኳይ ጊዜ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ዕቅድ የገንዘብ ድጋፍ የተካሄደ ነው፡፡ (ምንጭ፡- ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር)