የቅድመ ካንሰር ምርመራ በማድረግ የማህፀን በር ካንሰርን መታከም በበሽታ ደረጃ ላይ ሳይደርስ መከላከል እንደሚቻል ተገለጸ

የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ልየታና ህክምናን የተመለከተ የንቅናቄ አውደ ጥናት ተካሂደዋል፡፡

በአዳማ ከተማ በተካሄደው በዚህ አውደ ጥናት ላይ በመንግስት ተቋማትና በአጋር ድርጅቶች ውስጥ የካንሰር በሽታ ላይ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች፣ ከጎሳ መሪዎች እና ከሀይማኖት አባቶች የተውጣጡት ተሳትፈውበታል፡፡

በመድረኩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት በሚኒስቴሩ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ህይወት ሰለሞን የቅድመ ካንሰር ምርመራ በማድረግ የማህፀን በር ካንሰርን በተገቢው ጊዜ መታከም ከተቻለ በበሽታ ደረጃ ላይ ሳይደርስ መከላከል እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያደርሱት ተፅእኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ በመሆኑ በሽታዎቹን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ወ/ሮ ህይወት ተናግረዋል፡፡

ለማህፀን በር ካንሰር በሽታ እና የአኗኗር ሁኔታ ጋር ተያይዞ ለሚከሰቱ ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አጋላጭ የሆኑ መንስኤዎች እንዲሁም የመከላከያ መንገዶች ዙሪያ ተሳታፊዎች ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡ (ምንጭ፡-የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር)