ቀዳማይ የልጅነት ዕድገት መዳበር ላይ ትኩረት መሥጠት ለልጆች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገለጸ

ቀዳማይ የልጅነት ዕድገት መዳበር ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ልጆች ወደፊት ለሚኖራቸው ስኬታማ ህይወት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገልጿል፡፡

በቀዳማይ የልጅነት ዕድገትና መዳበር ላይ ያተኮረ ሃገር አቀፍ አውደ ጥናት ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ አውደ ጥናቱን ሲከፍቱ በጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው የጤና አገልግሎቶች ውስጥ የእናቶች እና ህጻናት ጤና አገልግሎት አንዱ መሆኑን ገልጸው በዘላቂ ልማት ግቦች የቀዳማይ የልጅነት እድገትና መዳበር ጉዳይ ትኩረት ማግኘቱን አስታውቀዋል፡፡

ዶክተር ሊያ አክለውም በቀዳማይ የልጅነት ዕድገትና መዳበር ላይ መስራት ልጆች ወደፊት ለሚኖራቸው ስኬታማ ህይወት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማድረጉም ባሻገር ለአገር እድገት፣ መረጋጋት እና ብልጽግና ቀጥተኛ አስተዋጽኦ ስላለው የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ውስጥ ከ5 ዓመት ዕድሜ ክልል በታች ካሉት ህጻናት ውስጥ 250 ሚሊዮን ያህሉ በአግባቡ እንክብካቤ ስለማይደረግላቸው በዕድሜያቸው መድረስ የሚገባቸው አካልና የአዕምሮ እድገት ደረጃ ላይ አይደርሱም፡፡

ከእርግዝና ጀምሮ ልጆች ከተወለዱ እስከ 8 ዓመት ድረስ የሚደረግ ሁሉን ያማከለ እንክብካቤ ለልጆች አካላዊ፣ አዕምሮአዊ እና ስነ-ልቦናዊ ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ ለአገርም ምርታማ ዜጋን ለማፍራት መሰረት ነው ተብሏል፡፡

ለሁለት ቀናት የሚመክረው በቀዳማይ የልጅነት ዕድገትና መዳበር ላይ ያተኮረው አውደ ጥናቱ በዘርፉ ላይ ለሚሰማሩና በህጻናት እድገት ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በመስራት ላይ ለሚገኙ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ለመፍጠር፣ በሴክተሮች መካከል ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከርና የቀዳማይ የልጅነት ዕድገትና መዳበርን በስፋትና በፍትሃዊነት ለማዳረስ ቁርጠኝነትን ለማረጋገጥና ሃብት ለማሰባሰብ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

አውደ ጥናቱ በጤና፣ በትምህርት፣ በሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና በአጋር ድርጅቶች በጋራ ትብብር የተዘጋጀ ነው፡፡ (ምንጭ፡-የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር)