በሞባይል የፅሑፍ መልዕክት አዘውትሮ መለዋወጥ ሲጋራ ማጨስን ለማቆም እንደሚረዳ ጥናት አመላከተ

በሞባይል ስልኮች የፅሑፍ  መልዕክት መለዋወጥን ማዘውተር ሲጋራን ለማቆም እንደሚረዳ አንድ ጥናት አመለከተ፡፡

ባሳለፍነው ማክሰኞ የቻይና ተመራማሪዎች ይፋ ያደረገው ይህ ጥናት በሞባይል ስልኮች አዘውትሮ  የፅሁፍ መልዕክት መለዋወጥ ሲጋራ ማጨስን ለማቆም መፍትሔ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ከፌረንጆቹ ነሐሴ 2016 እስከ ግንቦት 2017 ድረስ በተመረጡ 1 ሺህ 369 የሲጋራ ሱስ ተጠቂ በሆኑ የቻይና ወጣቶች ላይ ለ12 ሳምንታት የቆዬ ጥናት የተካሄደ ሲሆን በጥናቱ ወቅት ተጠቂዎቹ በሚያጨሱበት ጊዜ በሞባይል ስልኮቻቸው ላይ የተለያዩ የፅሁፍ መልዕክቶች በመላክ እንዲረበሹ ተደርጓል።

ከ12 ቀናት ቆይታ በኋላም 89 የሚሆኑት የሱሱ ተጠቂዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ማጨስ ያቆሙ ሲሆን 82 የሚሆኑት ደግሞ ከፍተኛ በሆነ ደረጃ ሱሱን መቀነስ መቻላቸው ነው የተገለጸው፡፡

ሌሎች 26 የሚሆኑ የሱሱ ተጠቂዎች ደግሞ ከችግሩ ለመላቀቅ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ  ላይ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

ይህ ውጤትም በሲጋራ ሱስ የተጠቁ ሰዎችን የምክር አገልግሎት በመሥጠት ድርጊቱን እንዲያቆሙ ከማድረግ በብዙ እጥፍ የሚሻል መሆኑን ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

ቻይና ሲጋራ በብዛት ከሚጨስባቸው ሀገራት ቀዳሚዋ ስትሆን በዓለም 40 በመቶ የሚሆኑት አጫሾች የቻይና ዜጋዎች መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ። (ምንጭ፡-ሲጂቲኤን)