አሜሪካ ኢትዮጵያ ለምታከናውነው የጤና ለሁሉም ፕሮግራም የ40 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ይፋ አደረገች

አሜሪካ ኢትዮጵያ እያከናወነች ለሚገኘው የጤና ለሁሉም ፕሮግራም የ40 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ በዛሬው ዕለት ይፋ ማደረጓ ተገለጸ፡፡    

ድጋፉ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ቀጣይነት እንዳለው የተገለጸ ሲሆን ኢትዮጵያ ጥራት ያለው መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ለዜጎቿ ለማዳረስ ለምታከናውናቸው ተግባራት አገልግሎት ላይ ይውላል ተብሏል፡፡   

ለዚህም የአሜሪካው ዓለም ዓቀፍ የልማት ድርጅት (USAID) በኢትዮጵያ የዘርፉን ፖሊሲ በማጠናከር እና የፋይናንስ አሠራር ማሻሻያዎች ዙሪያ ከኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር አብሮ እንደሚሠራም ነው የተገለጸው፡፡  

በኢትዮጵያ በማህበራዊ ጤና መድህን ፕሮግራም ቀደም ሲል በሠራቸው ሥራዎች ውጤታማ እንደሆነ የተነገረለት የአሜሪካው ዓለም ዓቀፍ ልማት ድርጅት አሁን ላይ ለ20 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን የማህበራዊ ጤና መድህን ዋስትና ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ነው የተገለጸው፡፡

ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ እንደሚደረግ የተገለጸው አዲሱ ፕሮግራምም ለጤናው ዘርፍ አገልግሎት የሀገር ውስጥ ሀብትን በመጠቀም፣ የጤና መድህን ዋስትናን በማስፋፋት ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግም ነው የተነገረው፡፡

የጤና ፋይናንስ እጥረትን በመቅረፍ ቀጣይነት ያለውና አስተማማኝ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ለዜጎቹ ለማዳረስ የሚያስችል መሆኑንም የተገለፀዉ፡፡ (ምንጭ: የአሜሪካ ኤምባሲ )