የመስማት እክል ያለባቸውን ሰዎች የሚያግዝ መሣሪያ ተለገሰ

የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር መቀመጫውን አሜሪካን ሀገር ካደረገው ስታርኪ ሂሪንግ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በአክሱም እና በመቀሌ ከተሞች ለሚገኙ የመስማት ችግር ላለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ለመስማት የሚያግዛቸውን የጀሮ ማዳመጫ መሣሪያ እርዳታ አደረገ፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የመስማት ችግር ላለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ካደረገው የጀሮ ማዳመጫ መሣሪያ እርዳታ በተጨማሪ ለህሙማኑ የምክር፣ የምርመራ እና የማከም አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረጉንም ገልጿል፡፡

በጆሮ ህክምና ዘመቻ ላይ ተሳትፎ ካደረጉት የህክምና ባለሙያዎች በተጨማሪ የምልክት ቋንቋ ተናጋሪዎች እና የበጎ ፍቃደኛ ተማሪዎች በመሣተፍ ዘመቻው ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን ድርሻ ተወጥተዋል፡፡

የጆሮ ህመም ህክምና ዘመቻው አምስተኛው ዙር ሲሆን በአዲስ አበባና በትግራይ ክልሎች እስካሁን ድረስ 7 ሺህ ለሚጠጉ ህሙማን አገልግሎቱ የተሰጠ ሲሆን ዘመቻው በቀጣይም በጅማ እና በድሬዳዋ በተመሣሣይ ሁኔታ እንደሚከናወን የፕሮግራሙ አስተባባሪ ዶክተር ጣዕመ እምባይ ሃደጉ ገልፀዋል፡፡

(ምንጭ፡-የጤና ሚኒስቴር)