የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ እያካሄደ ነው

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

ለ30ኛ ጊዜ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ “የአየር ንብረት ለውጥ ለ21ኛው የኢትዮጵያ ክፍለ ዘመን የህብረተሰብ ጤና ተግዳሮት’’ በሚል መሪ ቃል ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡

በጉባኤው መክፈቻ ስነ-ስርዓት የክሉን ፕሬዝዳንት በመወከል የተገኙት የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ መስፍን አሰፋ በሃገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ተከትሎ መንግስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሃገር ልማት ግንባታም ሆነ በህብረተሰብ ዕድገት መፋጠን ላይ ቁልፍ እና አዎንታዊ ሚና እንዳላቸው በቁርጠኝነት ያሳየበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከንቲባው የሙያ ማህበሩ የአባላቱን ሙያዊ ስነ-ምግባር በማጎልበት ለህብረተሰቡ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ በቅንነትና በታማኝነት መንፈስ እንዲያገለግል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በበኩላቸው የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ማህበር በጤና ፖሊሲው ትግበራ ተሳትፎ በማድረግ በጤናው ዘርፍ ለተመዘገቡት ውጤቶች የበኩሉን ጉልህ ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም ማህበሩ የአየር ንብረት ለውጥ በጤና ላይ ስለሚያደርሰው ችግር ትኩረት አድርጎ መወያየቱን አመስግነው በግብርና፣ በመሰረተ ልማት እና በሌሎች ዘርፎች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርሱ ችግሮች ሁሉ መገለጫቸው የጤና ቀውስ በመሆኑ የ30ኛው ጉባኤ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ መመረጡ ተገቢና ወቅታዊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ማህበር መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ለጤናው ዘርፍ ልማት እድገት አስተዋጽኦ ለማድረግ ቁርጠኛ ሆኖ እየሰራ መሆኑን የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍቅረዓብ ከበደ ገልጸዋል፡፡

ማህበሩ በጉባኤው ላይ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለሙያዎችና ድርጅቶች የዕውቅና ሽልማት አበርክቷል፡፡ 

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ማህበር ከ8 ሺህ በላይ የተመዘገቡ አባላት ያሉት ሲሆን ለሶስት ቀናት በሚቆየው ጉባኤው ለፖሊሲ አማራጭ በሚሆኑ ሃሳቦች ዙሪያ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ (ምንጭ፡-የጤና ሚኒስቴር)