የሰቆጣ ቃል-ኪዳን አፈጻጸምን የሚገመግም የመስክ ጉብኝት አሁንም ቀጥሏል

በሚንስትሮች፤ሚኒስትር ድኤታዎች፤የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎች እና የሚመለከታቸው የምግባረ ሰናይ ድርጅቶች ተወካዮች እየተደረገ ያለው የሰቆጣ ቃል-ኪዳን አፈጻጸምን የሚገመግም የመስክ ጉብኝት አሁንም ቀጥሏል፡፡

መንግስት ሐምሌ 2007 ዓ.ም በተካሄደው የፋይናንስ ለልማት አለም አቀፍ ስብሰባ ወቅት የሰቆጣ ቃል-ኪዳን (Seqota Declaration) በሚል የመቀንጨርን (Stunting) ችግር ከ2 ዓመት በታች የሚገኙ ህፃናት ቁጥር በ2022 ዓ.ም ዜሮ ለማድረስ ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወቃል፡፡

የቃልክዳኑን ይስራ አፈጻጸም ለመገምገም ከስድስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ሚኒስትሮች ፣ የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች እንዲሁም የልማት አጋሮች በተገኙበት በጋራ በመሆን በአማራ ብ/ክ/መ/ በላስታ ወረዳ በመገኘት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱም ጤና ኬላዎች፣ ሞዴል ቤተሰቦች፣ ት/ቤቶች፣ የግብርና ማዕከላት፣ የውሃ ፕሮጀክቶች የተጎበኙ ስሆን የተገኙ ውጤቶች እንዲሁም ያጋጠሙ ችግሮች ተለይተዋል፡፡ የመፍትሄ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል፡፡

የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት የመስክ ጉብኝት ቀጥሎ 549 ሺህ 831 ህዝብ በሚኖርባት ዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ተካሂዷል፡፡

ይህ የመስክ ምልከታ በጋግዚቭላ ወረዳ ቀበሌ 018 ለሙከራ የተተከለውን የሳተላይት ማሰራጫ ጣቢያ በመጎብኘት ነው የተጀመረው፡፡

የሳተላይት ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ እያደረገ ያለው ያዝሚ ድርጅት ተወካይ ስለ ቴክኖሌጂው ጠቀሜታ ሲያብራሩ በአጭር ጊዜ በበርካታ ጤና ኬላዎች፤ጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች የምግብ እጥረት እና አለመመጣጠን የሚያመጣውን ችግር በምን መልኩ ማስተካከል እንደሚቻል በሚሰጠው የቀጥታ ስርጭት ትምህርት መከታተል ይችላሉ ብለዋል፡፡

የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚን አማን በበኩላቸው በቴክኖሎጂው ከአዲስ አበባ በቀጥታ ስልጠና ማስተላለፍና በሁለት አቅጣጫ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ ሙከራ መደረጉን ጠቅሰው በቀጣይም ይህ ቴክኖሎጂ የሰቆጣ ቃልኪዳን የተገባባቸው በተከዜ ተፋሰስ ዙርያ በሚገኙ 33 ወረዳዎች ውስጥ ባሉ 900 ጤና ኬላዎች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል ብሏል::/የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር/