ሀገራዊ የጤና ዋስትና የትግባራ እቅድ ይፋ ሆነ

ሀገራዊ የጤና ዋስትና የትግባራ እቅድ ይፋ ሆነ፡፡

ሀገራዊ የጤና ዋስትና የትግባራ እቅዱ በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች፣ በእርስ በእርስ ግጭትና ወረርሽኝ በሽታ ለተጎዱ ሀገራት ድጋፍ ለማድረግ የሚረዳ እንደሆነ ተገልጿል።

የዓለም ጤና ድርጅት ኢትዮጵያ ባለፉት ጊዚያት በዘርፉ ያስመዘገበችውን ውጤትና የጤና ዋስትና ትግበራ እቅድ ይፋ መሆንን አድንቋል።

በሀገራዊ የጤና ዋስትና ትግባራ አቅድ መክፈቻ ፕሮግራም ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማንና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተግኝተዋል።

እቅዱ ይፋ የሆነበት ስነ ስርዓት ሲከፈት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር እቅዱ ድንገተኛ አደጋዎች ሲገጥሙ በቀላሉ ለመቋቋም የሚረዳ በመሆኑ አስፈላጊና ወቅታዊ መሆኑን ገልጸዋል።

በተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት በፍጥነት አሁን ያሉበትን ደረጃ በመፈተሸ ወደ ተሟላ መርሃ ግብር እንዲገቡ ለማድረግ መንግስት የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።

የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በበኩላቸው እቅዱን ወደ ተግባር ለማስገባት የተለያዩ ስራዎች መጀመራቸውን አስረድተዋል።

ይህን እቅድ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመተግበርም 300 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ መደረጉም ነው የተገለጸው።

ድጋፉ ከኢትዮጵያ መንግስት፣ መንግስታዊ ካልሆኑ አጋር ድርጅቶችና ሌሎች ቁልፍ ባለድርሻ አካላት እንደተገኘም ተጠቁሟል።

(ምንጭ፡- ኤፍ.ቢ.ሲ)