ወላጆች ከወለዱ በኋላ ለ6 ዓመታት ያክል በቂ እንቅልፍ እንደማያገኙ አንድ ጥናት አመለከተ

ወላጆች ልጅ ከወለዱ ከ4 እስከ 6 አመታት በቂ እንቅልፍ እንደማያገኙ አንድ ጥናት ያመለከተ ሲሆን በተለይ ይህ ችግር በእናቶች ላይ እንደሚበረታ ተነግሯል፡፡

ልጆቻቸውን ጡት የማያጠቡ እናቶችም እንኳን ቢሆኑ ከወንዶቹ ጋር ሲነጻጸር እንቅልፍ ማጣታቸው በእጅጉ እንደሚልቅ ተጠቅሷል፡፡

ጥናቱ የተካሄደው እ.ኤ.አ ከ2008 እስከ 2015 ባለው ጊዜ ውስጥ ለ4 ሺህ 650 ወላጆች ቃለ መጠይቅ በማድረግ ነው፡፡

አዳዲስ ወላጆች ሕፃናቱ ከተወለዱ በኋላ ባሉት 6 ወራት በቂ እንቅልፍ እንዳላገኙ ሲያስተውሉ ይደነግጣሉ ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ሕፃናቱ ለመዋዕለ ሕጻናት እስኪዘጋጁ ድረስ ወላጆች የእንቅልፍ እርካታቸውና መደበኛ የእንቅልፍ ጊዜአቸው ስለማይስተካከል ተስፋ እንደሚቆርጡ ተነግሯል፡፡

ጥናቱን ያቀረቡት ዩናይትድ ኪንግደም ዋርዊክ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሳካሪ ሌሞላ እንዳሉት ልጆች ለወላጆች የደስታ ምንጭ ሆነው ሳለ የመጀመሪያ ልጃቸውን ከወለዱ በኋላ እስከ ስድስት ዓመታት ድረስ በቂ እንቅልፍ አለማግኘት እና ከወላጅነት ጋር የተያያዙት ወሳኝ ሀላፊነቶችን ይጨምራሉ፡፡

ልጆችን በየቀኑ በተመሳሳይ ሰዓት ማስተኛትና መጽሐፍ ማንበብ እንዲሁም መደበኛ ተግባሮችን መከወን በቂ እንቅልፍ ለማግኘት ይረዳልም ተብሏል፡፡ (ምንጭ፡-ዴይሊ ሞኒተር)