በአፋር ክልል የኩፍኝ በሽታን ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት የተጠቂዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው

በአፋር ክልል አንዳንድ ወረዳዎች የተከሰተውን የኩፍኝ በሽታ ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት የተጠቂዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን የክልሉ ጤና ቢሮ አሰታወቀ::

በቢሮዉ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ኬዝቲም አስተባባሪ አቶ አብዱ አሊ እንደገለጹት ካለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ በአፋር አውሲ-ረሱ ዞን ሶስት ወረዳዎች በ16 ቀበሌዎች ውስጥ  የኩፍኝ በሽታ ተከስቷል።

በሽታው በተከሰተባቸው አይሳኢታ፣  ዱብቲና አፋምቦ ወረዳዎች 462 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውንና  የአራት  ሰዎች ህይወት ማለፉን አመልክተዋል።

“በሽታው ህፃናት በመደበኛነት መውሰድ የሚገባቸውን የመከላከያ ክትባት ሳይወስዱ በመቅረታቸውና ከስነ- ምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ሰውነታቸውን የበሽጻ መከላከል አቅም በመቀነሱ ምክንያት የተከሰተ ነው ብለዋል፡፡

በሽታውን ለመቆጣጠር የክልሉ ጤና ቢሮ የህክምና ግብአቶችን በማቅረብና የመከላከያ ክትባቶችን በመደበኛና በዘመቻ መልክ ከ15 ዓመት በታች ዕድሜ ላላቸው ልጆች እየሰጠ ነው።

በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ በበሽታው ተይዘው በቀን በአማካይ ወደ ጤና ተቋማት ይመጡ የነበሩ ህሙማን ቁጥር ከ20 ወደ 3 ሰዎች ዝቅ ብሏል ።

የአፋምቦ ወረዳ ዋና አሰተዳዳሪ አቶ ሁሴን አሊ እንደገለፁት በወረዳው ተከስቶ የነበረው የኩፍኝ በሽታ በህብረተቡ ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በመከላከልና የህክምና አገልግሎት በመስጠት እንዲቀንስ ማድረግ ተችላል ።

ከዚህ በፊት በቀን እስከ 10 የሚደርሱ ሰዎች በበሽታው ተይዘው ወደ ጤና ጣቢያ ለህክምና ይመጡ እንደነበር አስታውሰው “በአሁኑ ወቅት ግን ከ2 የሚበልጡ አይደሉም “ብለዋል ።

በሽታውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የቤት ለቤት ክትባት እየተሰጠ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

የኩፍኝ በሽታ ህፃናትን በከፍተኛ ትኩሳት እንዲጠቁና በሰውነታቸው ላይ ሽፍታ እንዲወጣ በማድረግ ለህመምና ለሞት ጭምር የሚያጋልጥ ነው ተብሏል። (ምንጭ፡-ኢዜአ)