ኢንዶኔዥያ በተከሰከሰው ቦይንግ ማክስ 737 የሟቾች ቤተሰቦች በቦይንግ ካሳ ተጭበርብረናል አሉ

ባለፈው ዓመት ኢንዶኔዥያ ውስጥ በተከሰከሰው ቦይንግ ማክስ 737 ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሰዎች በቦይንግ የካሳ ክፍያ መጭበርበራቸውን ጠበቃቸው ተናገሩ።

ጠበቃው ቤተሰቦቹ ቦይንግን እንዲሁም ላየን ኤርን እንዳይከሱ የሚከለክል ሰነድ እንዲፈርሙ ተደርገዋል ነው ያለው።

ሁለት አውሮፕላኖች ከተከሰሱ በኋላ ቤተሰቦች ቦይንግን መክሰስ እንዳይችሉ የሚያደርጉ ስምምነቶች እንደፈረሙ ቢቢሲ ደርሶበታል። ስምምነቶቹ በአደጋው የሞቱ ሰዎች ቤተሰቦች ቦይንግን አሜሪካ ውስጥ እንዳይከሱ ያግዳል ነው የተባለው።

ቦይንግ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፍቃደኛ አይደለም።

ባለፈው ዓመት ከኢንዶኔዥያ መዲና ጃካርታ የተነሳው ቦይንግ 737 ማክስ በረራ ከጀመረ ከ13 ደቂቃ በኋላ ተከስክሶ 189 ተሳፋሪዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

የሟቾች ቤተሰቦች በኢንሹራንስ አማካይነት ካሳ የቀረበላቸው አደጋው ከተከሰተ ከሳምንታት በኋላ ነበር።

የካሳ ገንዘቡን ለማግኘትም ቤተሰቦቹ ስምምነት መፈረም የነበረባቸው ሲሆን፣ ስምምነቱ ቦይንግን ወይም ላየን ኤርን ከመክሰስ የሚያግዳቸው እነደነበር ተገልጿል።

በአደጋው ባለቤቷን ያጣችው ሜርዲያን ኦገስቲን እንደምትለው፤ የኢንሹራንሱ ጠበቆች የመክሰስ መብቷን እንድታነሳ የሚያደርግ ሰነድ እንድትፈርም ገፋፍተዋታል።

"ሰነዶች እንድፈርም ሰጡኝ፤ ሰነዶቹ ካሳ መውሰድ ብችልም ላየን ኤርንና ቦይንግን መክሰስ እንደማልችል ይገልጻሉ።"

ሰነዱን ከፈረመች ከአንድ ወይም ከሁለት ሰዓት በኋላ ገንዘቡን እንደምታገኝ ገልጸውላት ነበር።

"ገንዘቡን ወስደሽ ሕይወትሽን ቀጥይ አሉኝ፤ እኔ ግን አልፈልገውም ነበር። ለእኔ ሚዛን የሚደፋው ገንዘቡ ሳይሆን የባለቤቴ ሕይወት ነው።"

ሜርድያን ሰነዱን ባትፈርምም ወደ 50 ቤተሰቦች እንደፈረሙ ይታመናል። እያንዳዳቸው የሚያገኙት ከ74 ሺህ ዩሮ በታች ካሳ ነው። በኢንዶኔዥያ ሕግ ቤተሰቦች 71 ሺህ ዩሮ ካሳ የማግኘት መብት ስላላቸው ካሳው አከራካሪ ሆኗል።

ከሟቾች ቤተሰቦች የጥቂቱ ጠበቃ ሳንጂቭ ሳይኝ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ቤተሰቦች መብታቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ ግፊት ተደርጎባቸዋል።

"የፈረሙት ቤተሰቦች ክፍያው አልተሰጣቸውም። የኢንሹራንሱና የኢንሹራንሱ አማካሪዎች አጭበርብረዋቸዋል። በዚህም የተጠቀመው ቦይንግን ነው" ብለዋል።

ቤተሰቦቹ በሚሊየን ዶላር የሚቆጠር ካሳ የማግኘት መብት ነበራቸው። ቦይንግ መሰል አይነት ሰነዶች በማስፈረም ተጠቃሚ ሲሆን የመጀመሪያው እንዳልሆነም ተናግረዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2005፤ የቦይንግ ማክስ 737 ኢንዶኔዥያ ውስጥ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ተከስክሰሶ 149 ሰዎች ሞተዋል። የሟቾች ቤተሰቦች ቦይንግን አሜሪካ ውስጥ ላለመክሰስ ስምምነት ተፈራረመው ነበር። ቦይንግ ማክስ 737፤ 2007 ላይ ተከስክሶ 102 ሰዎች ሲሞቱም ተመሳሳይ ስምምነት ተፈርሞ ነበር።

አንድ ስሙ ያልተጠቀሰ የኢንሹራንስ ጠበቃ በሦስቱም ስምምነቶች እጁ እንዳለበት ተገልጿል።

ሳንጂቭ ሳይኝ እንደሚሉት፤ የቦይንግን የቀደሙ ሰምምነቶች ከግምት በማስገባት፤ ቦይንግ ከላየን ኤር አደጋ በኋላ የሟቾችን ቤተሰቦችም አስፈርሟል ተብሎ ይታመናል።

"ቦይንግ ሰነዶቹ ስለመፈረማቸው መረጃው የለውም ለማለት ይከብዳል። ለስምምነቱ ተባብረው ይሆናል የሚል ጥያቄም ያስነሳል"

ቦይንግ ስለነዚህ ስምምነቶችና ስምምነቶቹን ስላቀነባበረው ኢንሹራንስ ጠበቃ መረጃ እንዳለው ተጠይቆ ምላሽ አልሰጠም። ሆኖም፤ "ቦይንግ የሰዎች ሕይወት በመጥፋቱ ጥልቅ ሀዘን ይሰማዋል። ከደንበኞቹና ከበበራው ዘርፍ ጋር በመሆን ተጎጂዎች እንዲያገግሙ ይጥራል። በእንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች እንደሚደረገው፤ የቦይንግ ኢንሹራንስ ከሌሎች ኢንሹራንሶች ጋር እየተመካከረ ነው" ብሏል።

የላየን ኤርና የቦይንግ ኢንሹራንስ የእንግሊዙ 'ግሎባል ኤሮስፔስ' ሲሆን፣ 'ግሎባል ኤሮስፔስ' የቀረበበትን ክስ ባይቀበልም፤ የደንበኞችን ሚስጥር ማውጣት አይቻልም በሚል በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

"የበረራ ኢንሹራንስ በአንድ አደጋ ውስጥ የተሳተፉ ከአንድ በላይ አካላት መወከል ይችላል። የተለያዩ ደንበኞችን ጉዳይ በተናጠል እያየን፤ ተገቢ ባልሆነ መንገድ መረጃ እንዳይሰራጭም እያደረግን ነው" ብሏል።

እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ አየር መንገድንና የአውሮፕላን አምራችን ለወደፊት ከመከሰስ መከላከል የተለመደ ነውም ብሏል።

ቦይንግ፤ ማክስ 737 አውሮፕላን ተከስክሶ (የኢትዮጵያ አየር መንገድና ላየን ኤር) ሕይወታቸውን ላጡ ሰዎች ቤተሰቦች የ100 ሚሊየን ዶላር ካሳ እንደሚሰጥ ባለፈው ሳምንት መግለጹ ይታወሳል።

የቤተሰቦቹ ጠበቆች ስለ ገንዘቡ ዝርዝር መረጃ እንዳልደረሳቸው ገልጸዋል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)