የአፍሪካ አገራት አህጉራዊ የህክምና ስምምነትን እንዲያፀድቁ ጥሪ ቀረበ

የአፍሪካ ኤክስፐርቶችና ፖሊሲ አውጪዎች በአፍሪካ የህክምና መሳሪያዎች አቅርቦትን ያሻሽላል የተባለውን የአፍሪካ የህክምና ኤጀንሲ ስምምነት እንዲያፀድቁ ለአፍሪካ ሃገራት ጥሪ አቀረቡ፡፡

ጥሪውን ያቀረቡት የአፍሪካ ህብረት በጤና ፣ስነህዝብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ላይ ባካሄደው የአፍሪካ የሚኒስትሮች ጉባኤ ወቅት ነው፡፡

የአፍሪካ ህብረት ማህበራዊ ጉዳዮች ኮሚሽነር አሚራ ኤል ፋዲል እንደተናገሩት የአፍሪካን ህክምና ኤጀንሲ ስምምነት በፍጥነት ፀድቆ ወደ ትግበራ እንዲገባ ህብረቱ ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡

አህጉራዊ ስምምነቱ እስካሁን ድረስ ሶስት አፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት አልጄሪያ ፣ ሩዋንዳ እና ሳሃራዊ የፈረሙ ሲሆን፤ አርብ ማዳጋስካር አራተኛ ፈራሚ አገር በመሆን ስምምነቱን እንደተቀላቀለች ታውቋል፡፡

ስምምነቱን በአንድ ጊዜ 15 የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት አፀድቀው ወደ ተግባር ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዥንዋ በድረ ገፁ አስነብቧል።

በአፍሪካ ህብረት ማህበራዊ ጉዳዮች ኮሚሽን ድጋፍ የአፍሪካ የመድኃኒት ኢንዱስትሪ ደንቦችን ለማቋቋም በሚሰሩ ስራዎች ላይ ሌሎች የአፍሪካ መንግስታት ወደ ስምምነቱ መቀላቀል እንዳለባቸው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ጥሪ አቅርበዋል።

ኮሚሽነሯ በአህጉሪቱ ያሉትን የጤና ችግሮች ለመፍታት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በስምምነቱ እንዲሳተፉ የማወያየት እና የማስተዋወቅ ስራ ይቀጥላል ብለዋል።

ግብፅ አህጉራዊ ማዕከል ለማቋቋም በሂደት ላይ የምትገኝ ሲሆን ብሄራዊ የክትባት ስትራቴጂዎችን እንዴት ማጎልበት እና ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል ስልጠና ይሰጣል ሲሉ የጤና ሚኒስተሯ መናገራቸውን በዘገባው ተካቷል።

በአፍሪካ አንዳንድ ሀገራት 26 በመቶ የሚሆኑት ብቻ የክትባት ዕድል የሚያገኙ ሲሆን ማዕከሉ የክትባት ሽፋንን በየዓመቱ ቢያንስ በ10 በመቶ የማሳደግ ዓላማ እንዳለው የተገለጸ ሲሆን አጠቃላይ ግምባታው በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።