ቮልቮ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መኪናዎችን በ2019 ለገበያ እንደሚያቀርብ አስታወቀ

ቮልቮ የተባለው የመኪና አምራች ኩባንያ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ የመኪና ሞዴሎችን እኤአ በ2019 ለገበያ እንደሚያቀርብ ገልጿል፡፡

ከቀን ወደ ቀን እያደገ የመጣውን የመኪና ፍላጎትን ለማርካት በርካታ ኩባንያዎች የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም መኪና የማምረት ሥራውን ተያይዘውታል፡፡  ኩባንያዎች   በልጦ ለመገኘትም የተለያዩ ሞዴሎችን ይፋ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

የመኪና ምርቱ በፍጥነት ቢያድግም በየጊዜው ወደ ገበያ የሚቀርቡና ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሸከርካሪዎች ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡

መሠረቱን ስዊድን ያደረገውና እኤአ በ2010 በቻይናው የቤት መኪና አምራች ኩባንያ ጂሊ የተገዛው ቮልቮ የተባለው የመኪና አምራች ኩባንያ እ.ኤ.አ ከ2019 ጀምሮ የሚያመርታቸው የመኪና ምርቶች ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ፣ በግማሽ ኤሌክትሪክ የሚሠሩና በትንሽ ነዳጅ ብዙ ኃይል በማመንጨት መስራት የሚችሉ የመኪና ሞዴሎችን ይፋ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡

ኩባንያው እ.ኤ.አ በ2025 ጠቅላላ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መኪናዎችን ወደ 1 ሚሊዮን ገደማ   ለገበያ ለማቅረብና ለመሸጥ እቅድ ይዟል፡፡

ይህ መሰረቱን ስዊድን ያደረገው የመኪና አምራች ኩባንያ ላመርታቸው ነው ብሎ ከዘረዘራቸው የመኪና ሞዴሎች በተጨማሪ ቀደም ሲል ሲያመርታቸው የነበሩትን የመኪና አይነቶችን ማምረቱን እንደሚቀጥል ነው የተገለፀው፡፡

ዋና መቀመጫውን ቻይና ያደረገው ጂሊ በ2010 ኩባንያውን ከገዛው ጊዜ አንስቶ አዳዲስ ሞዴሎችን ለማምረት ከፍተኛ ወጪ ሲያወጣ ነበር፡፡

እንደነ ማርቼዲስና ቢኤምደብሊው የመሳሰሉ ኩባንያዎች ከሚያመርቷቸው መኪኖች ጋር በጥራት ተወዳዳሪ ለመሆን በቅቷል፡፡ ከ2019 እስከ 2021 ድረስ ለገበያ የሚያቀርባቸው ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ አምስት የመኪና ሞዴሎችንም ይፋ አድርጓል፡፡

እነዚህ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚመረቱ መኪናዎች በአውሮፓና ቻይና በሚገኙ የኩባንያው  ፋብሪካ በተጨማሪም በአሜሪካም በመገንባት  የምርት መጠኑንና ጥራቱን ለማሳደግ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከፍተኛ አቅም ያላቸው በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሸከርካሪዎች ከመስራት ባለፈ ያለ ሰው የሚሽከረከሩ መኪናዎችን ለመስራትም በሂደት ላይ እንደ ሆነ ነው የተዘገበው፡፡

ከባለፈው ወር ጀምሮ ኩባንያው ትኩረቱን ወደ ከፍተኛ ውጤት የሚያስገኘው የኤሌክትሪክ መኪና ምርት በማድረግ ከነ ቴስላ እና ማቼዲስ ኤኤም ጂ ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡