ጣሊያን ስደተኞችን መቀበል እንደታከታት ገለጸች

የበርካታ ስደተኞች መዳረሻና መተላላፊያ የሆነችው ጣልያን ስደተኞችን መቀበል ታክቶኛልና እገዛ እፈልጋለሁ አለች፡፡

ጣሊያን ከሌሎች አገራት እገዛ  ካላገኘች ስደተኞች የሚተላለፉበትን ወደብ ለመዝጋት እንደምትገደድም አስታውቃለች፡፡ ኦስትርያ ለስደተኞች በሬን እዘጋለሁ ማለቷን ተከትሎ ከጣልያን ውግዘት ገጥሟታል፡፡

የበርካታ ስደተኞች ቀዳሚ ምርጫ የሆነችው ጣልያን ስደተኞችን መቀበልና ህይወታቸውን መታደጉ ታከተኝ ማለት ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡ በተለይም በሊቢያ አድርገው የሜድትራንያን ባህርን አቋርጠው ወደ ጣልያን የሚገቡ ስደተኞች ትልቁ የቤት ሥራዋ እንደሆነም ትገልፃለች፡፡

ወደ ጣልያን የሚጓዙ ስደተኞች ቁጥር በየጊዜው መጨመር አቅሟን እየተፈታተነው ይገኛል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እንዳስታወቀው እኤአ በ2017 የመጀመሪያ  ግማሽ ዓመት 85ሺ ያህል ስደተኞች ወደ ጣልያን ገብተዋል፡፡

ይህ አሃዝ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 20 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ሁለት ሚሊዮን ያህል ስደተኞችን ወደ ጣልያን በሚያርጉት ጉዞ ካሰቡበት ሳይደርሱ ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል፡፡  

አውሮፓን በመናፈቅ ከቀዬአቸው እየተፈናቀሉ ወደ ጣልያን ለመግባት በሚያደርጉት ጥረት በጀልባ መገልበጥና በመሰል ምክንያቶች ለችግር የሚጋለጡትን ህይወት ለመታደግ የምታደርገው ጥረት ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላት እንደሆነም ጣልያን ገልፃለች፡፡

ስድተኞች ጋር  በተያያዘ  የተፈጠሩ ያሉ ችግሮች  እየተባባሱ በመምጣታቸው ስደተኞችን መቀበልም ሆነ ህይወታቸውን የመታደጉ ሥራ እጅጉን ከብዶኛል ብላለች፡፡ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ችግሩን በመረዳት ድጋፋቸውን በተጨባጭ ማረጋገጥ እንዳለባቸውም በፅኑ እያሳሰበች ነው፡፡

ጥሪዋ አጥጋቢ ምላሽ ካላገኘች ስደተኞች የሚመላለሱበትን ወደብ ለመዝጋት እንደምትገደድም ነው በአፅንዖት የገለፀችው፡፡ ለድንገተኛ አደጋ ጊዜ በወደብ አቅራቢያ ያሰማራቻቸውን የነፍስ አድን ባለሙያዎችና መርከቦችንም ከአገልግሎት እንዲታቀቡ አደርጋለሁ ብላለች፡፡ 

ይህ ከመሆኑ በፊት የአውሮፓ ህብረትና አባል አገራቱ እንዲሁም ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ አቅርባለች፡፡

የጣልያን ጎረቤት የሆነችው ኦስትርያ በበኩሏ ከጣልያን ወደ አገሯ የሚገቡ ስደተኞችን ለመከላል ወታደራዊ ኃይል ለማሰማራት ማቀዷን ገልፃለች፡፡ በዕቅዷ መሰረትም ዘመናዊ የጦር ተሽከርካሪዎችና 750 ያህል ወታደሮች በተጠንቀቅ ቆመዋል፡፡

የኦስትርያ መከላከያ ሚኒስትር ወሃስ ፒተር ዶስኮዚል የሚዲትራንያን ባህርን በማቋረጥ ወደ ጣልያን የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ካልቀነሰ ወታደራዊ ኃይሉን የማሰማራቱ እርምጃ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ብረነር በሚባለው መተላላፊያ ቁጥጥሩ እንዲጠናከር እንደሚደረግም ነው አክለው የገለፁት፡፡

የቬናን ዕቅድ ሮም ክፉኛ ማውገዟን ሮይተርስ አስነብቧል፡፡ የጣልያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስትርያ ለስደተኞች በሯን ለመዝጋት የነደፈችውን ዕቅድ መተቸታቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡

የኦስትርያ እርምጃ በአውሮፓ ህብረት የተቀመጠውን በነፃነት የመንቀሳቀስ መብትን የሚፃር ነው ብለዋል፡፡