ቻይና የዓለም አቀፍ የሮቦቶች ኮንፈረንስን እያስተናገደች ነው

ቻይና የ2017ቱን አለም አቀፍ የሮቦቶች ኮንፈረንስን እያስተናገደች እንደምትገኝ  አስታወቀች ፡፡

ትላንት በይፋ የተከፈተው ኮንፈረንሱ በቤጂንግ ኢትሮንግ የኤግዚቢሽን ማዕከል እየተካሄደ ነው፡፡ ኮንፈረንሱ በዋነኝነትም የዓለምን የሮቦቶች የመሥራት አቅም ማሳደግ እና በተለያዩ የሮቦት ሰሪ ድርጅቶች ግንኙነት ማሳደግ ነው፡፡

የሮቦት አምራች ድርጅቶች ግንኙነት በማሳደግ ለተሻሉ የፈጠራ ውጤቶች እንዲተባበሩ ታስቦ የተዘጋጀ የአለም አቀፍ የሮቦቶች ኤግዚቢሽን በቻይና እየተካሄደ ነው፡፡

ከ150 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ድርጅቶች በተሳተፉበት በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ በፋብሪካዎች እና በቤት ውስጥ ሥራን ሊያቀሉ የሚችሉ እንዲሁም የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችሉ ሮቦቶች ታይተውበታል፡፡

በኢግዚቢሽኑ ላይ የህክምና ሥራዎችን የሚያቀሉ፣ የቤት ውስጥ ስራዎችን ሊያግዙ እና ሰዎችን ማዝናናት የሚችሉ በርካታ ሮቦቶች ታይተዋል፡፡

ከሮቦቶቹ ውስጥ ቲዮትሮኒኮ የተባለ ሮቦት በተሠሩለት 53 ጣቶች አማካኝነት ለመጫወት አስቸጋሪ የሆነውን በኤሌክትሪክ የሚሰራ የፒያኖ መሳሪያ በግሩም ሁኔታ በመጫወት የታዳሚዎችን ቀልብ ስቧል፡፡

ይህ ሮቦት ምንም አይነት ስህተት ሳይሰራ በአስገራሚ ሁኔታ መሳሪያውን መጫወት ቢችልም የኛ አላማ ሰዎችን የማገዝ ስራ እንዲሰራ እና ለመማሪያነት እንዲሆን ነው ሲሉ የሮቦቱ ሰሪዎች አባል የሆኑት ፒተር ቻንግ ገልጸዋል፡፡

 ቻንግ እንዳለው ፒያኖ መማር ለሚፈልጉ ሰዎች ቲዮ ለማስተማር ብቁ ነው ሲሉ አሁንም ግን የበለጠ ለማሻሻል እየሰራን ነው፡፡   

ካንቦት የተባለ የቻይና ኩባንያ ያመረተው አዲሱ ዮዮ ሮቦት ደግሞ በድምጽ እና በፊት እንቅስቃሴ ከሰዎች ጋር መግባባት የሚችል ሲሆን 22 መገጣጠሚያዎች ያሉት በመሆኑ ከቦታ ቦታ በቀላሉ መንቀሳቀስ ይችላል፡፡

ለሰው ልጅ እንደ ጓደኛ ሊሆን የሚችለው ሮቦት በውድ ዋጋ የቀረበ ሲሆን አሁን ላይ 32 ሺ ዶላር የተለጠፈበት ሲሆን በዋነኝነት ለባንኮች፣ ሙዚየም እና ለትላልቅ ገበያ ማዕከላት ጥሩ አገልግሎት ይሰጣል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ እንደነዚህ አይነት ሮቦቶች በተለያዩ መንገዶች እየተሰሩ ነው፡፡ ዮዮ ግን ለሠራተኞች የሚርቁ ወይም የማይመቹ ሥራዎችን ይሠራል፡፡

የካንቦት ኩባንያ የንግድ ኃላፊ የሆኑት ሊ ዶንግዶንግ እንዳሉት ዮዮ አሁን በገበያ ላይ ካሉ ተመሳሳይ ሮቦቶች በላይ መስራት የሚችል ሲሆን በርካታ ትእዛዞች ስላሉ በብዛት ማምረት ላይ ፈተና እያጋጠመን ነው ብለዋል፡፡

እንደ ዮዮ አይነት ሮቦቶች አሁን በስፋት በትምህርት ቤቶች እና ፋብሪካዎች ውስጥ ይሰራሉ፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪም የጃፓን ቴሌኮም ተቋም የጃፓንን ባህል መሰረት አድርገው የቀብር ስነ ስርአትን ማከናወን የሚችሉ ሮቦቶችን ፈጥረዋል፡፡

እነዚህ ሮቦቶችም በቡድሂዝም እምነት የሃይማኖት አባቶች የሚያከናውኑትን ስራ በቅናሽ ዋጋ ያከናውናሉ፡፡ ቢሆንም ግን በጃፓን አንዳንድ ሰዎች ይህንን የቴክኖሎጂ ውጤት እየተቃወሙት ይገኛሉ፡፡( ምንጭ:  ሲ ጂ ቲ ኤን )