አለም አቀፉ ማህበረሰብ በአሳሽ ሳተላይቶች ዙሪያ ተባብሮ መስራት ይገባዋል–ፕሬዝደንት ሺ ጂንፒንግ

የቻይናዉ ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ አለም አቀፉ ማህበረሰብ በአሳሽ ሳተላይቶች ዙሪያ ተባብሮ መስራት ይገባዋል ሲሉ ጥሪ አቀረቡ።

ፕሬዝደንት እንደተናገሩት አለም አቀፉ ማህበረሰብ የአሳሽ ሳተላይቶችን ጠቀሜታ ተገንዝቦ ለጋራ ተጠቃሚነት ተባብሮ መስራት ይገባዋል። ከዛም ባለፈ ለሳተላይቶቹ ተግባራዊነት አለም አቀፍ ይዘት እንዲኖረዉ መስራትም ጠቀሜታዉ ጉልህ እንደሆነ ገልጸዋል።

ፕሬዝደንት ሺ ይህንን ያሉት በሰሜን ምዕራብ ቻይናዋ ሻንዢ ግዛት እየተካሄደ ላለዉ 13ኛዉ የአለም አቀፍ የአሳሽ ሳተላይት ጉባኤ መክፈቻ በላኩት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸዉ ነዉ።

ፕሬዝደንቱ አክለዉም አሳሽ ሳተላይቶች ለህዋ ጥናትና ምርምር ወሳኝ መሳሪያዎች ከመሆናቸዉም ባለፈ አለም አቀፉ ማህበረሰብ አከባቢዉንም ሆነ የሚኖርበትን አለም እንዲረዳ የሚያስችሉ በመሆናቸዉ ለማህበራዊ ልማት ጠቀሜታቸዉ የጎላ ነዉ ብለዋል።

የሳተላይቶቹ ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ፕሬዝደንት ሺ ሀገራቸዉ ቻይናም ብትሆን ለዘርፉ እድገት ትኩረት ሰጥታ በመስራቷ ባለፉት 40 አመታት ዉስጥ ስኬታማ ስራዎችን ሰርታለች ብለዋል።

በዚህም ቻይና BDS የተሰኘ የአሳሽ ሳተላይት ስርዓት በመዘርጋት አመርቂ ስራ በመስራት ላይ ነች ነዉ ያሉት።  

ቢዲኤስ የተሰኘዉ ስርዓት ከዚህ አመት መጠናቀቅ አስቀድሞ ለአከባቢዉ ሀገራት ግልጋሎት መስጠት ይጀምራል ያሉት ፕሬዝደንቱ በአውሮፓዊያኑ 2020 ደግሞ በአለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ይሆናል ብለዋል። ከዛ በተጨማሪ ግን ከ2035 አስቀድሞ እጅግ ቀልጣፋና የዘመነ የአሳሽ ሳተላይት ስረዓት እንደሚዘረጋ ፕሬዝደንት ሺ ቃል ገብተዋል።

ለተሻለ የሰዉ ልጆች ህይወትና ምቹ የሆነች አለምን ለመፍጠር ሰዎች መረጃና ሀሳብን መለዋወጥ ይገባቸዋል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።

50ኛዉ አመት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሰሳና ጥናቶችን ለበጎ አላማ የማዋል ኮንፈረንስ በዚህ አመት እንደሚከበርም ዘገባዉ አስታዉሷል። (ምንጭ፡-ሲጂቲኤን)