በማህበራዊ ድህረ ገፅ በሚሰራጩ ሀሰት ወሬዎች ሀገራት ያልተፈለገ ቀውስ ውስጥ እየገቡ ነው ተባለ

በማህበራዊ ድህረ ገፅ የሚሰራጩ የሀሰት ወሬዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ በመምጣታቸው ሀገራት ያልተፈለገ ቀውስ ውስጥ እየገቡ ነው ተባለ፡፡

ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በአለም ላይ በአሁን ሰአት ከ3 ቢሊዮን በላይ ህዝብ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚ ነው፡፡ ይህም በአለም ውስጥ ከሚገኘው ህዝብ ውስጥ 40 በመቶው የሚሆነው ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ መሆኑን እንደሚያሳይ አጥኝዎቹ ይገልጻሉ፡፡

ይህ ቁጥር በፍጥነት እያደገ ሲሆን በተለይም በማደግ ላይ ባሉ እንደ አፍሪካ ባሉ አህጉራት ውስጥ በሚገኝ ሀገራት የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቁጥር በየአመቱ 20 በመቶ እየጨመረ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ከዚህ ቁጥር ውስጥ ከፍተኛውን የሚይዘው ታዲያ ፌስቡክ ነው፡፡ በአሁን ሰአት በአለም ላይ ከ2 ቢሊዮን በላይ ሰዎች የፌስብክ ተጠቃሚዎች ሲሆኑ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ በየአመቱ ፊስቡክን ለመጠቀም አዲስ አካውንት የሚከፍቱ ናቸው ተብሏል፡፡

ፊስቡክ ቀዳሚውን ይያዝ እንጅ ዩቲዩብ፣ ኢንስታግራም፣ ቲዎተር፣ ዋትስአፕ፣ እስናፕቻት እና ዊ ቻት ከፍተኛ ተጠቃሚ ያላቸው የማህበራዊ ትስስር ገፆች ናቸው፡፡

ታዲያ በእነዚህ የማህበራዊ ትስስር ገፆች የሚሰራጩ መረጃዎች አሁን አሁን ከእውነታ የራቁ በመሆናቸው ዜጎችን ላልተፈለገ ሽብር እየተዳረጉ እነደሆነ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡

በተለይም የማህበራዊ ትስስር ገፆችን የሚጠቀሙት እድሜያቸው ከ15 እስከ 39 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው አብዛኛዎቹ ድህረ ገፆቹን የሚከፍቱት እና መልዕክት የሚለዋወጡት በእጅ ስልኮቻቸው በመሆኑ ማናቸውንም ጉዳዮች እንደ ትክክለኛ መረጃ ለሰዎች ሰለሚያጋሩ ትክክል ያልሆኑ መረጃዎች በቀላሉ ለሰዎች ይደርሳሉ፡፡

ይህ ብቻ አይደለም ፈፅሞ ያልተከሰተና ከጉዳዩ ጋር የማይገናኙ ምስሎችንና ቪዲዮዎችን በዚያ ሰፍራና ሰአት የተከሰተ በማስመስል ለሰዎች በማጋራት ሰዎችን ለግጭት እየዳረጉ በመሆናቸው ይህንን መለየት የሚያስችል መተግበሪያ በተደጋጋሚ ለሙከራ ቢቀርብና በተወሰነ መልኩ ወደ ስራ ቢገባም ችግሩን በሚፈለገው ልክ መፍታት ስልለተቻለ እያንዳንዱ ሀገር የራሱን መፍትሄ መውሰድ አለበት ነው የተባለው፡፡

መረጃው በቅርቡ በናይጀሪያ በሀሰተኛ መረጃ ምክኒያት የተከሰተውን የእርስ በእርስ ግጭት እንዲሁም በዋትስ አፕ ላይ በተነዛ ሐሰተኛ ወሬ ምክንያት ተቃጥለው የተገደሉት የሜክሲኮ ዜጎች ጉዳይ አንስቶ ጉዳዩ እንደ ቀላል የሚታለፍ ሳይሆን ሁሉም የአለም መንግስታት ሽብርተኝነትን ከመዋጋት ባልተናሰሰ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል ሲል ያነሳል፡፡ (ምንጭ፡- ቢቢሲ)