ቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ በጨረቃ ምስጥራዊ እና ጨለማ ክፍል ሰው አልባ መንኮራኩር ልታሳርፍ ነው

ቻይና በጨረቃ ምስጥራዊ እና ጨለማማ ክፍል ‹‹ቻንግ-ኢ- 4›› የተሰኘች ሰው አልባ መንኮራኩር ለማምጠቅ የመጨረሻ ዝግጅቷን ማጠናቀቋን አስታውቃለች፡፡

መንኮራኩሯ የፊታችን እሁድ ህዳር 30 ከሲቹሀን የጠፈር ጣቢያ ተነስታ በጨረቃ ደቡባዊ ዋልታ ጨለማማ ክፍል ታርፋለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ምስጥራዊው እና ሩቅ የተባለውን የጨረቃ ክፍል ከመሬት ሆኖ ለመመልከት የተሰወረ እንደሆነም ተገልጸዋል፡፡

በመንኮራኩሯ ላይ በጨረቃ ምህዋር እየዞረ መረጃ የሚያደርስ አሳሽ ሳተላይት እና በጨረቃ ጨለማማ ክፍል አርፎ የሚያስስ መሳሪያ ይካተታሉ ነው የተባለው፡፡

ሳተላይቱ በጨረቃ የሚካሄደውን አሰሳ እና ምርምር የሚመራ እንዲሁም ወደ መሬት ስለ ሂደቱ መረጃ የሚያደርስ ነው፡፡

ሳይንሳዊ ተልዕኮው የጨረቃን ላይኛው ክፍል፣ በውስጧ የያዘቻቸው የማዕድን አይነት እና ይዘት ይመረምራልም ተብሏል፡፡

ከዚህ ባሻገር የጨረቃን ዝግመተ ለውጣዊ ታሪክ በማጥናት የመሬትን እና ሌሎች ፕላኔቶች አፈጣጠር ለመረዳት ያስችላል ተብሏል፡፡

በጨረቃ ጨለማማ ክፍል እፅዋት መብቀል እንደሚችሉ ለማረጋገጥ ሙከራ እንደሚያካሂድና በዚህም የእፅዋት ዝርያዎች እና የነብሳት እንቁላሎች ይላካሉ፡፡

በጨረቃ አነስተኛ የስበት መጠንና አስቸጋሪ የአየር ፀባይ እንዲሁም በኮንቴነር በተዘጋጀ ሰው ሰራሽ አየር ፀባይ እፅዋትን ለማብቀል ይሞከራልም ተብሏል፡፡

በአውሮፓዊያኑ 2019 ‹‹ቻንግ ኢ- 5›› የተሰኘች ሌላ መንኮራኩር ሙከራ የተካሄደባቸውን የእፅዋት እና ነብሳት ናሙና ውጤት ወደ መሬት ይዞ ለመምጣት ይህች መንኮራኩር ትላካለች ስትል ቻይና አስታውቃለች፡፡

ቻይና ወደፊት በጨረቃ ላይ የሰው መኖሪያ መንደር ለማቋቋም ዕቅድ ያላት ሲሆን ለዚህ እቅድ መሳካት በቅድሚያ የሰው ሰራሽ የእፅዋት ምህዳር መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ከሙከራው ጠቃሚ ግብዓት እና ልምድ ይገኝበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ተልዕኮው በረጅም ጊዜ ሂደት የሰውን ልጅን በማርስ እና ጨረቃ ላይ ለማኖር ለሚደረገው ጥረት የመጀመሪያ እርምጃ መሆኑም ተገልጿል፡፡ (ምንጭ፡- ዴይሊ ሜል)