ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ የስራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ የስራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ አስተባባሪነት በ20 ዘርፎች የቴክኖሎጂ ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ተጠናቆ በትግበራ ሂደቱ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገበት ነው፡፡

4ቱ ፍኖተ ካርታዎች ደግሞ በዝግጅት ላይ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡ 

ፍኖተ ካርታው የአለም ሀገራት ተሞክሮዎችን በመቀመር ኢትዮጵያ ወደፊት በቴክሎጂው ዘርፍ የምትጓዝበትን አቅጣጫ የሚስያቀምጥ ነው ተብሏል፡፡

በዚህ አመት የቴክኖሎጂ ፍኖተ ካርታው 10 ከመቶ እንዲተገበር እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው፡፡

በ2 አመት ውስጥ 2 ሺህ የቴክኖሎጂ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን፣ 20 ሺህ የቴክኖሎጂ የስራ ዕድልን እና 2 ቢሊዮን ዶላር ቴክኖሎጂ ሀብት መፍጠር የሚያስችል አስቻይ ሁኔታን የሚፈጥረው 2፣2፣2፣2 መርሃ ግብር የዚህ አካል መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ ገልጸዋል፡፡  

የቴክኖሎጂ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም የሰው ኃይል መፍጠርም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል፡፡

በአለም ላይ ኢኮኖሚውን እየመሩ ካሉ 10 ተቋማት ውስጥ ስምንቱ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያሉ ሲሆን አንዱ በነዳጅ አንዱ ደግሞ በባንክ ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው፡፡ (ምንጭ፡-የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር)