የቻይና ሳይንቲስቶች በአምስት ሰከንድ ውስጥ ኃይል የሚሞላ የተንቀሳቃሽ ስልክ ባትሪ ሠሩ

የቻይና ሳይንቲስቶች በአምስት ሰከንድ ውስጥ ኃይል የሚሞላ የተንቀሳቃሽ ስልክ  ባትሪ መሥራታቸውን አስታውቀዋል። 

ተንቀሳቃሽ  ስልኮች በስፋት አገልግሎት ላይ ከዋሉበት ጊዜ ጀምሮ ሰዎች የእጅ ስልኮቻቸውን በቀላሉ  ከቦታ ቦታ ይዘው ስለሚንቀሳቀሱ እና ለአገልግሎትም ምቹ በመሆናቸው በስፋት ጥቅም ላይ ይውላሉ በመሆኑም  ባትሪዎቻቸው ቶሎ ቶሎ መጨረሳቸው የተለመደ ነው፡፡

ታዲያ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ሲባል በተለይየ ጊዜ በአዳዲስ ፈጠራ በመታገዝ የተለያየ መፍትሄ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡

ከሰሞኑ ደግሞ ቻይናውያን ሳይንቲስቶች በአምስት ሰከንድ ውስጥ በኤሌክትሪክ ሃይል የሚሞላ የተንቀሳቃሽ ስልክ ባትሪ መስራታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

ይህ አዲስ ፈጠራ በቻይናው ዥዣንግ ዩኒቨርስቲ ኢንጅነሪንግ ዲፓርትመንት ተመራማሪዎች የተሰራ ሲሆን ይህ ባትሪ ከአልሙኒየም መሰል ውህደቶች የተሰራ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሀይሉን መልሶ መጠቀም የሚያሰችል በመሆኑ ቀድሞ ከምናውቀው የባትሪ አይነት 91 በመቶ የተሻለ አቅም እና ጥራት እንዳለው ተጠቁሟል፡፡

የአንድን ስልከ ባትሪ ሙሉ ለማድረግ አምስት ሰከንድ ብቻ ወሰደ ማለት በቀን 10 ጊዜ እንኳን ቻርጅ ብናደርግ የዚህ ባትሪ እድሜ ወይም የአገልግሎት ዘመኑ 70 አመታት እንደሆነ ነው ተመራማሪዎቹ የጠቆሙት፡፡  

ምንም አገልግሎት ላይ ያልነበረን ስልክ ለማሰነሳት አዲሱ ባትሪ የሚፈጅበት አንድ ሰከንድ ብቻ ነው ተብሏል፡፡

አዲሱ ባትሪ ከፍተኛ ሙቀት እና ቅዝቃዜንም የመቋቋም ከፍተኛ ችሎታ ያለው ሲሆን ከ40 ዲግሪ ሰልሺየስ እስከ 120 ዲግሪ ሰልሺየስ ድረስ የነበረውን አቅም መጠቀም ይችላል ተብሏል፡፡  

አዲሱ ባትሪ አሁን ያለውን ኃይል እንዲላበስ ተመራማሪዎች ሊቲየም አዮን የተጠቀሙ ሲሆን ከፍተኛ የሆነ ሀይል እና የኤሌክትሪክ ንዝረት እንዲኖረው መደረጉንም ገልፀዋል፡፡

ይህ አዲስ ፈጠራ በቅርቡ ለገበያ የሚውል ሲሆን ከተንቀሳቃሽ ስልክ በተጨማሪ በኤሌክትሪክ ለሚሰሩ ተሸከርካሪዎችና ለሌሎች ነገሮች አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡ /ሲ ጂ ቲ ኤን/