አየር መንገዱ ስማርት ስልክን በመጠቀም ብቻ የቅድመ በረራ አገልግሎትን ማግኘት የሚያሰችል አሰራር መጀመሩን አስታወቀ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘመናዊ የዲጅታል ቴክኖሎጅ በመተግበር ስማርት ስልክን በመጠቀም ብቻ የቅድመ በረራ አገልግሎትን ማግኘት የሚያስችል አሰራር መጀመሩን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ግዙፍና ስኬታማ አየር መንገድ በመሆኑ በተደጋጋሚ ጊዜ  የእውቅና ሽልማቶችን ሲቀበል ቆይቷል፡፡

ሆኖም ግን እስከአሁን በነበረዉ አሰራር ተገልጋዮች ጉዞ በሚያደርጉበት ሰዓት በረራቸዉን ለማረጋገጥ ማለትም የቅድመ በረራ አገልግሎት ለማግኘት ምቹ የሆነ የቴክኖሎጂ አሰራር ባለመኖሩ ረጃጅም ሰልፎችን ለመጠበቅና የተለያዩ እንግልቶች ሲዳረጉ መቆየታቸው ይነሳል፡፡

አሁን ግን አየር መንገዱ አሰራሩን ለማዘመንና በቀላሉ ለተገልጋዮች በሚፈልጉበት ሰዓት እና ባሉበት ቦታ ስማርት ስልኮቻቸዉን በመጠቀም የበረራ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል አሰራር መዘርጋን ገልጿል፡፡

አሁን ላይ አየርመንገዱ የጀመረዉ የቅድመ በረራ አገልግሎት መስጫ አሰራር ወይም ቸክ ኢን አገልግሎት ተገልጋዮች በቀላሉ በግል ስማርት ስልኮቻቸዉ ለራሳቸዉ አገልግሎት የሚሰጡበት ከመሆኑም በተጨማሪ የቅድመ በረራ አገልግሎት ለማግኘት ረጅም ሰልፍ መጠበቅን እንዲሁም እንግልትን የሚያስቀር እንደሆነ ነዉ የተገለፀዉ፡፡

አገልግሎቱን ለማግኘት በስማርት ስልክ እና የአየርመንገዱን ድረ ገፅ በመጠቀም ብቻ ባሉበት ማግኘት የቅድመ በረራ አገልግሎት ከማግኘት በተጨማሪ መንገደኞች የጎዞ ቲኬታቸዉን በአየር መንገዱ ድረገፅና በሞባይል ላይ በተጫነዉ የአየር መንገዱ መተግበሪያ ማግኘት ይችላሉ ተብሏል፡፡

የአየርመንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም አየር መንገዱ ተገልጋይ ተኮር እንደመሆኑ በዚህ በዋና መስሪያ ቤቱ በአዲስ አበባ አየር መንገድ ፈጣን የደንበኞች የቅድመ በረራ አገልግሎት መስጫን በዘመናዊ የቴክኖሎጅ አሰራር በመዘርጋታችን ደስታ ይሰማናል ብለዋል፡፡

በራስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ቴክኖሎጅን በመጠቀም ዘመናዊ የዲጂታል አሰራር መጀመሩ ተገልጋዮች በራሳቸዉ የቅድመ በረራ አገልግሎታቸዉን እንዲያዉቁ ከማስቻሉም በተጨማሪ ረጃጅም ሰልፎች ላይ ተራ ይዞ መጠበቅንና እንግልትን የሚያስቀር ነዉ ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የመንገደኞች የቅድመ በረራ አገልግሎት መስጫ አሰራር ምቹ የሆነ የጉዞ አገልግሎትን ከመስጠት ባሻገር ተጓዦች ትኬት ለመግዛት፣ በኦንላይን ክፍያ ለመፈፀምና የቅድመ በረራ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑ በቀጣይም ይህ አሰራር ተጠናክሮ የሚቀጥል ነዉ ሲል አየር መንገዱ በላከልን መግለጫ አመላክቷል፡፡