በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የስራ እድል ለመፍጠርና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በዘርፉ ለመደገፍ እየተሰራ ነው

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሥራ እድል ለመፍጠርና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በዘርፉ ለመደገፍ እየተሠራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያን ዲጂታላይዝ ለማድረግ በተጀመረው እንቅስቃሴ የዘርፉ ምሁራን እገዛ ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ በሚኒስቴሩ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ውይይቱ የቴክኖሎጂ ምሁራንን ለመፍጠርና በዘርፉ የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ የሚችሉበትን መንገድ ለማመላከት ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከተለያዩ ተቋማት የመጡ የስራ ሃላፊዎች የተቋማቶቻቸውን የስራ እንቅስቃሴ የተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ የተቋማቸውን የሥራ እንቅስቃሴና የወደፊት እቅድ ለተሳታፊዎቹ ያብራሩ ሲሆን በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የስራ እድል ለመፍጠርና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በዘርፉ ለመደገፍ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኢኖቬሽን አማካሪ ካውንስል ጋር በመተባር ባዘጋጁት በዚህ የውይይት መድረክ ከአሜሪካ፣ ከእንግሊዝና ከፈረንሳይ የመጡ የቴክኖሎጂ ምሁራን ጨምሮ ከሀገር ውስጥ ከየዘርፉ የተውጣጡ ኃላፊዎች ተሳትፈውበታል፡፡

ተሳታፊዎቹ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላቸውን ልምድ በመጠቀም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ፣ ትኩረት ሊደረግባቸው በሚገቡ ዘርፎችና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ ሃሳቦችን በማንሳት ተወያይተዋል፡፡ (ምንጭ፡-የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር)