የኢትዮጵያውያንን የፈጠራ ሃሳቦችንና ስራዎችን በአለም አቀፍ ደረጃ በነፃ ለመመዝገብና ለመጠበቅ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

የኢትዮጵያውያንን የፈጠራ ሃሳቦችንና ስራዎችን በአለም አቀፍ ደረጃ በነፃ ለመመዝገብና ለመጠበቅ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ፡፡

‹‹ሴቭ አይዲያ›› የተሰኘው ድርጅት የኢትዮጵያ የፈጠራ ስራዎችን ለመመዝገብና ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችለውን ስምምነት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ተፈራርሟል፡፡

ሰምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሹመቴ ግዛው እና ‹‹የሴቭ አይዲያ›› መስራችና ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ሃዝቦ ሾኮ ፈርመውታል፡፡

ሴቭ አይዲያ የተሰኘው ድርጅት በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የፈጠራ ስራዎችን በነፃ የሚመዘግብ፣ የሚጠብቅ፣ ሃሳቦቹ ወደ ስራ እንዲገቡ ከባለሃብቶች ጋር የማገናኘት ስራ የሚሰራና ራሱም የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ድርጅት ነው፡፡ 

ስራዎቹን በኦንላይን ለህዝብ ክፍት በማድረግ እንዲተዋወቁ የማድረግ ስራ የሚሰራው ድርጅቱ በአፍሪካ ውስጥ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያ፣ ኬንያ፣ አይቮሪኮስትና ቦትስዋና እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡ 
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሹመቴ ሚኒስቴሩ ‹‹በዲዛይን ኢትዮጵያ›› ውድድር ወቅት የቀረቡ የኢትዮጵያውን የፈጠራ ሃሳቦች አለም አቀፍ እውቅና ኖሯቸው እንዲጠበቁና ወደ ስራ እንዲገቡ ፍላጎት እናዳለው ገልጸዋል፡፡

‹‹ሴቭ አይዲያ›› የአፍሪካ ቢሮውን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚከፍት ፕሬዝዳንቱ ፕሮፌሰር ሃዝቦ ሾኮ በስምምነቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡ (ምንጭ፡-የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር)