በሶስት አውታር ማተሚያ(3ዲ-ፕሪንት) አማካኝነት ቤቶችን ገንብቶ መንደር መመስረት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሊሆን ነው፡፡
በዚህ ቴክኖሎጂ የሚገነባው መንደር በዝቅተኛ ወጪ እና በአነስተኛ ጊዜ ቤቶችን ገንብቶ በማጠናቀቅ በአለም የቤት አልባ ሰዎችን የመጠለያ ችግር ለመፍታት ያለመ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
የሶስት አውታር ማተሚያ ላለፉት አስርት ዓመታት በህክምና፣ ኮንስትራክሽን፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በሌሎች ዘርፎች ፈርቀዳጅ አዳዲስ የፈጠራ ግኝቶችን በማቅረብ የሰዎችን ህይወት እያቃለለ እንደሆነ ይነገራል፡፡
በቤቶች ልማት ዘርፍ ደግሞ በአውሮፓዊያኑ 2013 አንድ የቻይና ኩባንያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶስት አውታር ማተሚያ የተገነባ አንድ ቤት ይፋ እንዳደረገ ተጠቅሷል፡፡
አሁን ላይ ደግሞ አንድ ሲዊዘርላዳዊ ታዋቂ የቤት ንድፍ አውጪ ዋይቭስ በሀር ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በዘላቂነት የሰዎችን የቤት ችግር ለመፍታት መቃረቡን አስታውቋል፡፡
የቤት ንድፍ አውጪው አዲስ የፈጠራ ቴክኖሎጂ በማከል በዝቅተኛ ወጪ እና በአጭር ጊዜ ተጠናቀው የሚገነቡ ቤቶችን ለተጠቃሚ ማቅረብ እንደሚቻል ተናግሯል፡፡
እንደመነሻም ቴክኖሎጂው በላቲን አሜሪካ በሚገኙ ሀገራት ተግባራዊ መደረግ እንደሚጀምርም ተጠቁሟል፡፡
በዚህም በሜክሲኮ፣ አይቲ፣ ሳልቫዶርና ቦሊቪያ ላይ በሚገነቡ 2 ሺህ 200 ቤቶች ላይ ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ለማድረግ ውጥን መያዙን ተመልክቷል፡፡
የሶስት አውታር ማተሚያ በመደበኛው አሰራር የሚወጣውን የቤት ግንባታ ወጪ ከግማሽ በታች የሚቀንስና ቤቶቹም በአንድ ቀን ተገንብተው እንዲጠናቀቁ የሚያደርግ አዲስ ቴክኖሎጂ ነው መባሉን ሲኤንኤ ሌግዠሪ ዘግቧል፡፡