ራዕይህ ህያው ነው!!

ክፍል አንድ
አባ መላኩ

የኢትዮጵያ ሕዳሴ መሃንዲስና የለውጥ ሀዋርያ፤ ታላቁ መሪ በተለሙት መስመር በመጓዝ የኢትዮጵያን ሕዳሴ ለማብሰር ተግተን እንሰራለን፤ ታላቁ መሪ የቀየሱልንን የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ራዕይ እንዲሳካ ጠንክረን እንሰራለን፤ ባለራዕዩ መሪ እንደሻማ ቀልጠው የቀየሱልንን ታላቅ ራዕይ እንዲሳካ  ጠንክረን እንሰራለን፤ ሁሌም የሚታወስ ብልህ መሪ – ዛሬም በልባችን አለህ!! እያለ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሁሉም አቅጣጫ ድምጹን እያሰማ ነው። የታላቁን መሪ መለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት አራተኛ ዓመትን በማስመልከት። 

እርግጥ ነው፤ ዛሬ ኢትዮጵያ ማስመዝገብ የቻለቻቸው ድንቅ ስኬቶች ሁሉ ላይ የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ አሻራዎች በጉልህ አርፈውባቸዋል። አቶ መለስ አገራችን የመልቲ ፓርቲ ሥርዓትን በመከተል ዴሞክራሲያዊ እንድትሆን አድርገዋል፤ አገራችን ፌዴራላዊ መንግሥት እንድትሆን በማድረግ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩና ህዝቦች በመረጧቸው ተወካዮቻቸው እንዲተዳደሩ፣ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን እንድያጎለብቱ አድርገዋል፤ በድህነትና ጦርነት ትታወቅ የነበረችን አገር በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የምታስመዘግብ አገር እንድትሆን አብቅተዋታል፤ በስንዴ ልመና ትታወቅ የነበረች አገር ዛሬ ላይ በምግብ ሰብል ራሷን እንድትችል አድርገዋል፤ አገራችን በምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ  የዲፕሎማሲ የበላይነት እንዲኖራት በማድረግ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ  መድረኮች ተሰሚነት እንዲኖራት አድርገዋል፤ አገራችን የአረንጓዴ ልማት አራማጅ እንድትሆን አድርገዋታል። ታዲያ እኛ ኢትዮጵያዊያኖች የእኚህ ታላቅ ሰው  ትልቅ ውለታ አለብን። 

ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ዓለም ያደነቃቸው ታላቅ መሪ ነበሩ። የዓለም ታላላቅ መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ኢኮኖሚስቶች፣ የጥበብ ሰዎች ወዘተ ሳይቀሩ አድናቆታቸውን ቸረዋቸዋል።  እኚህ ታላቅ ሰው  በሞት ሲለዩ  የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ እንዲሁም የዓለም ህዝብ  በጥልቅ የሃዘን ስሜት እንዲዋጥ አድርገዋል፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ ከወጣትነት እድሜያቸው ጀምረው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለአገራቸውና ለህዝባቸው ሰርተዋል። ሥራቸውም ውጤታማ ሆኖ ዓለም ስለ አገራችን  መልካም መልካሙን መመስከር ችሏል።

ኢትዮጵያ ማስመዝገብ የቻለቻቸው ስኬቶች መሃንዲስ የሆኑት መለስ ዜናዊ ድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩን ከህጻን እስከ አዛውንት በጥልቀት አዝኗል። ሁሉም ያዘነው ከኚህ ታላቅ ሰው ተጠቃሚ ስለነበር ነው። በወቅቱ አንዳንዶች በተለይ ጽንፈኛው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ህዝቡ ሐዘኑን ሲገልጽ ተገዶ እንደሆነ  በማስመሰል ሲገልጹ ነበር። እነዚህ ጽንፈኛ አካላትም ቢሆኑ የፖለቲካ ትርፍ ያስገኝልናል ብለው እንጂ እውነታውን አጥተውት አልነበረም። ካፈርኩ አይመልሰኝ በሚል የተሳሳተ አካሄድ እውነታውን መሸምጠጥ የትም አያደርስም። ህዝብን አስገድደህ አደባባይ ማሰባሰብ ይቻል ይሆናል። ይሁንና በምንም ተዓምር በእንባ ልታራጨው ግን ከቶ አይቻልም።  

ለሕዝብ አሳቢ፣ ብልህና ቆራጥ የሆኑት መለስ ዜናዊ ሕልፈተ ህይወት የኢትዮጵያዊያን ብቻ ሐዘን አልነበረም፡፡ ሕዝብን ከድህነት ማላቀቂያ ራዕያቸውን የተጋሩ፣ አስተዋይ አዕምሯቸው ባፈለቀው ሃሳብ ተጠቃሚ የሆኑ አፍሪካዊያንም ጥልቅ ሐዘናቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል። ከሰሞኑ የእኚህን ታላቅ ሰው አራተኛ ሙት ዓመት አክብረናል።  

የዛሬ አራት ዓመት የእኚህ ታላቅ የኢትዮጵያ መሪ  ህልፈተ ህይወት ሲሰማ መላው ዓለም ያለውን አክብሮት የገለፀው እጅግ በተለየ መልኩ ነበር። በተመሳሳይ ታላላቅ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃኖችም ሳይቀሩ ስለ አቶ መለስ  ብዙ ብለዋል።  በዚህ የመጀመሪያ ክፍል ጽሁፌ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በወቅቱ በዘገባዎቻቸው ካቀረቧቸው መካከል ጥቂቶቹን እንደሚከተለው አቀረብኳቸው፡፡
ጃኮብ ዙማ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት፤ ለአፍሪካና ለኢትዮጵያ ህዝብ በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ የነበሩ፣ በተካፈሉበት መድረክ ሁሉ የተለየ ብቃት ያላቸውን ታላቅ ሰውን ማጣት እጅግ አሳዛኝ ነው። አቶ መለስ ዜናዊ ለአገራቸው ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ጭምር ጠንካራ መሪ ነበሩ።  

ኤለን ጆንሰን የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት፤ መለስ ዜናዊ የኢኮኖሚ ለውጥ መሪ፣ የአህጉሪቱ ምሁር መሪ ነበሩ። በአካባቢያዊ ስብሰባዎች ላይ ከአፍሪካ ዕድገት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ላይ የተለየ ምሁራዊ አቅምና ብቃት ያላቸው በመሆናቸው ቀዳሚ ነበሩ። 

ባርናባ ቤንጃሚን የደቡብ ሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስትር፤  ለደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ህዝብና ለምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ እጅግ በጣም አሳዛኝ ቀን ነው። አቶ መለስ ታላቅ መሪ ነበሩ፡፡ በአጎራባች አገራት ሠላም እንዲሰፍን ሁሌም የሚተጉ  ነበሩ። እኛ በደቡብ ሱዳን የምንኖር በተለይ ኢትዮጵያንና አቶ መለስ ዜናዊን ምንጊዜም ወዳጃቸውን የማይከዱ በመሆናቸው እንደ አጋራችን እናስባቸዋለን። በመሆኑም በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሞት አዝነናል። 

ጀስ ማኑኤል ባሮሶ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት፤ መለስ ዜናዊ የተከበሩ የአፍሪካ መሪ ነበሩ። ለዓመታት ከራሳቸው አገር ህዝብ በተጨማሪ በአጠቃላይ የአፍሪካን ህዝብ ኑሮ ለማሻሻል በአፍሪካ ህብረት፣ በአየር ንብረት ለወጥ፣ በልማት፣ በሠላምና መረጋጋትን ዙሪያ በመሥራት በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያረጋገጡ መሪ ነበሩ። ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ መዳበር፣ ለሰብዓዊ መብት መከበር፣ ለህዝብ ብልፅግና እንዲሁም ለሌሎች ለአካባቢው አገራት መረጋጋትና ትስስርን የጀመረችውን ሥራ አጠናክራ እንደምትቀጥል እተማመናለሁ።

ዴቪል ካሜሮን የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩ፤  መለስ ዜናዊ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የአፍሪካ ልሣን የነበሩ እንዲሁም ለሶማሊያና ሱዳን አመራርና ራዕይ የለገሱ መሪ ነበሩ።
ለኢትዮጵያ ልማት በተለይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ከድህነት በማውጣት ለአገራቸው ያበረከቱት አስተዋጽኦ ለአካባቢው ተምሣሌት ሆኗል። አሁን አቶ መለስን አጥተናቸዋል። 

ቶኒ ብሌር የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ አቶ መለስ በተለይ አገራቸውን ከአስከፊ ድህነት ወደ ኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት እንዲሸጋገር በመምራታቸው በኢትዮጰያ ታሪክ ውስጥ የጎላ ሥፍራ ያላቸው መሪ ናቸው። 

ባራክ ኦባማ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት፤ አቶ መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያ ዕድገት፣ በተለይ  ደሆች ኢትዮጵያዊያንን ከድህነት ለማውጣት ባላቸው ተነሳሽነት እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል። በጂ – 8 አገራት ስብሰባ ላይ በተገናኘንበት ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠር ኢትዮጵያውያንን በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ከድህነት ለማውጣት ላላቸው ፍላጎት በግሌ ያለኝን አድናቆት ገልጬላቸው ነበር። ከዚህ በተጨማሪ አቶ መለስ ዜናዊ ለአፍሪካ ሠላምና ደህንነት ላበረከቱት አገልግሎት፣ ለአፍሪካ ህብረት መጠናከር ላደረጉት አስተዋፅኦ፣ አፍሪካን በመወከል በዓለም አቀፍ መድረኮች ላሰሙት ድምፅ ታላቅ አክብሮት አለኝ። የኢትዮጵያ መንግሥት ለልማት፣ ለዴሞክራሲ፣ ለአካባቢያዊ ሠላምና መረጋጋት፣ ለሰብዓዊ መብት መከበር፣ ለህዝብ ብልፅግና የሚያደርገውን ጥረት እናበረታታለን።

ባን ኪሙን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ፤ መለስ ዜናዊ በተለየ የአመራር ብቃታቸው የአፍሪካን ጉዳይ በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ በማከናወን እንዲሁም ባስመዘገቡት የኢኮኖሚ ዕድገት የሚታወሱ ታላቅ መሪ ናቸው፡፡

ኦሊሴንጎነ ኦባሳንጆ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት የአቶ መለስ ዜናዊ ሞት አፍሪካ ደፋርና ባለራዕይ መሪዋን የተነጠቀች ያህል የሚቆጠር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት መለስ ዜናዊ ሞት አፍሪካን ቁርጠኛ፣ ሩቅ አሳቢ፣ ባለራዕይና ደፋር መሪ አሳጥቷታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በዛሬይቱ አፍሪካ አንፀባራቂ ከሆኑት መሪዎች አንዱ ነበሩ፡፡ በአፍሪካ ሕብረት ያሳዩትን ስኬታማ ሥራ አስተውያለሁ፡፡ መለስ ብልህ በመሆናቸው የአፍሪካ መሪዎች እኔም ጭምር የአፍሪካ ህብረትንና የኔፓድን ፕሮግራም እንዲያዘጋጁ ወስነን ሰጥተናቸው ነበር፡፡ ሞታቸው በጣም አስደንጋጭ ዜና ነው የሆነብኝ፡፡

ኢስማኢል ኦማር ጉሌህ የጅቡቲ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት፤ የጅቡቲ ታላቅ ወንድም የሆኑትን የአቶ መለስ ዜናዊን በሞት መነጠቅ የሰማነው በከፍተኛ ሐዘን ነው፡፡ አቶ መለስ አገራቸውን በአፍሪካ አህጉር ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያላት አገር እንድትሆን ለማስቻል ያደረጉት ጥረት ፍሬ መስጠት ጀምሯል፡፡ መለስ የተነሳሽነትና የቁርጠኝነት አርአያ በመሆን ሽብርተኝነትንና ፀብ አጫሪነትን በጀግንነት በመዋጋት ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡ በአቶ መለስ ሞት አፍሪካ ካሏት ድንቅ ልጆች አንዱን አጥታለች፡፡

ዩዌሪ ሙሴቪኒ የኡጋንዳ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት፤ የመለስ ዜናዊ ሞት ኢትዮጵያ ላይ ብቻ የደረሰ አሳዛኝ ጉዳት ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ትልቅ ጉዳት ነው፡፡ መለስ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንድነትና አገሪቱን በኢኮኖሚ ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ባበረከቱት አስተዋፅኦ ሁሌም ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡ ለአህጉሪቱ ሠላምና መረጋጋት እንዲሁም ለኢኮኖሚ ዕድገት በሚደረገው ትግል ውስጥ ታላቁን አስተማማኝ አጋር ተነጥቀናል፡፡

ሙዋዪ ኪባኪ የኬንያ ፕሬዚዳንት፤ በኬንያ ሕዝብና መንግሥት ስም በአቶ መለስ ዜናዊ ሞት የተሰማኝን ጥልቅ ልቅ ሀዘን ለቤተሰቦቻቸው፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት እገልፃለሁ፡፡ መለስ ዜናዊ አገራቸውን በማረጋጋትና በኢኮኖሚ በማሳደግ ረገድ ተጨባጭ ሥራ ያከናወኑና ባለራዕይ መሪ ነበሩ፡፡

የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ አዲንጋ፤  መለስ ዜናዊ ታላቅ መሪ፣ ምሁር፤ የፓን አፍሪካኒዝም አራማጅ ነበሩ። አቶ መለስ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደዕድገት ለማሸገገገር ባደረጉት ጥረት ዘወትር የሚታወሱ መሪ ናቸው።

የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ ኮፊ አናን፤  የአቶ መለስ ዜናዊ በሕይወት አለመኖር ለኢትዮጵያ ፈታኝ ነው፡፡ የሥልጣን ሽግግሩ የተረጋጋና ሠላማዊ እንደሚሆን እንዲሁም ኢትዮጵያ የሕዝቧን ፍላጎት የሚያንፀባርቅና ልዩ የሆነችውን አገር እምቅ አቅም የተገነዘበ መሪ እንደሚኖራት ተስፋ አደርጋለሁ ነበር ያሉት። ሌሎችስ ምን ብለው ነበር። በቀጣዩ የሁለተኛ ክፍል ጽሁፌ ይዤ እቀርባለሁ።