ናይጀሪያ የቦኮ ሃራም መሪዎችን መግደሏን አስታወቀች

አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 18 /2008 (ዋኢማ)- የናይጀሪያ ጦር በርካታ የጽንፈኛው ወታደራዊ መሪዎችን መግደሉን አስታወቀ።

የጦሩ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደገለፁት፥ ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ በፅንፈኛው ቡድን ላይ መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት ተሰንዝሯል፡፡ በዚህም በርካታ የቡድኑን መሪዎች መግደል ተችሏል።

በአየር ጥቃቱ የቡድኑ መሪ አቡ በክር ሼኩ ትከሻው ላይ ክፉኛ መቁሰሉን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡

የአየር ጥቃቱ የቡድኑ ጠንካራ ይዞታ እንደሆነ በሚነገረው በሰሜን ምስራቅ ብሮኖ ግዛት አካባቢ የተፈጸመ እንደሆነም ቢቢሲ አስታውቋል፡፡

በተወሰደ የአየር ጥቃት ምን ያክል የቡድኑ መሪዎች እንደተገደሉ የተገለጸ ነገር የለም።

ቦኮ ሃራም በናይጀሪያ በተለይም በሰሜናዊው የሀገሪቱ ክፍል ሰፊ ግዛትን መቆጣጠሩ ይታወቃል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በናይጀሪያ እና በጎረቤት ሀገር መንግስታት በሚደርስበት ጥቃት ሳቢያ በርካታ ይዞታዎቹን እያጣ ነው ተብሏል።

በቅርቡ ናይጄሪያን የጎበኙት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ቦኮ ሃራምን ከምረቱ ለመንቀል መስራ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን በአፍሪካ የቢቢሲ ዘጋቢ ካይ ቶሚ ኦላዲፖ አስታውቋል፡፡

ቦኮ ሃራም የናይጄሪያን መንግስት በኃይል በመጣል እስለማዊ መንግስት ለመመስረት እየጣረ የሚገኝ አሸባሪ ድርጅት ነው፡፡ በርካታ የናይጄሪያ ወጣት እንስቶችን በማገት እያሰቃየ መሆኑ ይታወቃል፡፡