አስተዛዛቢው የግብጾች ነገረ-ስራ (ክፍል ሁለት)

                                

 

እንግዲህ ከማጠቃለሌ በፊት የማያወላዳ ምላሽ የሚያስፈልገውን አንድ ጥያቄ ማንሳትና መመለስ ተገቢ መስሎ ይሰማኛል፡፡ ስለዚህ ታዲያ መላው የሀገራችን ህዝቦች ለዘላቄታዊ የጋራ ዕጣ ፈንታ ህዝባችን መቃናት ሲሉ እጅጉን ስር አከስደደው ድህነትና   ከሁዋላቀርነት ጋር የሞትሽረት ትግል የገጠሙበትን ታሪካዊ እውነታ ‹‹ የኢትዮጵያ ህደሴ ጉዞ ›› እያልን መጥራታችን በዚህን ያህል መጠን የሚያስበራግጋቸው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከግብጽ ሽፍጠኛ መንግስት የቀረበ ወዳጅ እንዲኖራቸው ይጠበቃልን? ደግሞስ ሕገመንግስታዊ ስርአቱን በአመጽ ተግባር ለመናድ ቆርጠው መነሳታቸውን ደጋግመው ሲነጋገሩ የሚደመጡት የትምክህት እና የጠባብ ብሐርተኝነት ፅንፈኛ አስተሳሰብ አራማሾቹ ቡድኖች ይልቁንም ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል በጊዜያዊ ጥቅም እየደለሉ አይደል አንዴ ለሀገር አውዳሚው የጥፋት ተልእኮቸው ማስፈፀሚያ እያደረጉት ያሉት? ታዲያ እነርሱ አንደልብ ሲራጩት የሚስተዋለው ገንዘብ ትክክለኛ ምንጩ ከየት ሊሆን ይችላል? እንደኔ እንደኔ ግን ብሩን የሚያገኙት አንደተባለውም ከሽፍጠኞቹ ግብፃውያን ፖለቲከኞችና ሊፕሎማቶች እንጂ ከሌላ ሀገር መንግስት ሊሆን አይችልም ባይ ነኝ፡፡

ይህን የምልበት ምክንያት ምንም እንኳን ሻዕቢያ መላሹ የአስመራ አገዛዝ አንደማይተኛልን ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ቢሆንም፣ ግን ደግሞ አሁን ለራሱ በቋፍ ላይ እንደሚገኝ ተደጋጋሞ የተነገራለት የኤርትራ መንግስት የኛን ታቃዋሚዎች በዚህን ያህል መጠን ገንዘብ ያንበሸብሻቸዋል ብሎ መጠርጠር ኢ.ምክያታዊ ይሆናልና ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ኢትየጵያ ውስጥ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ያለውን ሀገር አቀፍ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንናድወጣ ያስገደደንን የሁከትና ብጥብጥ ተግባር ከመጠንሰስ አስከ ማንቀሳቀስ ጉልህ ሚና የተጫወተ የውጭ ሃይል ቢኖር የግብጽ መንግስት ነው ብሎ መደምደም ነባራዊውን ሀቅ የገናዘበ አጥጋቢ ማጠቃለያ እንጂ በምንም መመዘኛ ሊስተባበል የሚችል ጉዳይ አይመስለኝም፡፡

ይህን ካለኩኝ ዘንዳም፣ ለመሆኑ ከግብጾቹ ጋር በሚዶልቱት  ፀረ- ኢትየጵያ እቺን ሀገር አተራምምሰው ፈርጀ ብዙ የህዳሴ ጉዞዋን የማምከን ዕኩይ ተልዕኮ ለመፈፀምና ለማስፈፀምም ጭምር ቆርጠው የተነሱት ፅንፈኛ ተቃዋሚዎችስ የትኞቹ ናቸው? አውን ከዚህ አኳያ የለየለትን የሀገር ክህደት ተግባር መፈፀም የያዘው ራሱን ‹‹ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ›› እያለ የሚጠራው ኦነግ ብቻ ነውን? ወይስ ደግሞ ግንቦት ሰባትን የመሳሰሉት በተለይም በአማራ ክልል ህዝብ ስም ለመነገድ የሚቀጣውን ትምክህተኛ ፖለቲካዊ እሳቤ የሚያቀነቅኑት  የተቃውሞው ጎራ ሀይሎችም ጉዳይ የማስፈፀሙን አኩይ ተልዕኮ ተቀብለው እየተንቀሳቀሱ ይሆን ? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳትና በፊትሽ አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት ሌላው የዚህ ወቅት አንገብጋቢ የቤት ስራችን ነው ብየ አምናለሁ፡፡

ከነዚህ  ከነዚህ ሽብርተኛ ተብለው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተፈረጁ  ነውጠኛ ቡድኖች ጋር በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የሚገለጽ ቁርኝት ያላቸውና እዚህ አገር ውስጥ ተቀምጠው የጥፋት ተልእኮውን ለማሳካት  ይህን ያህል እጅግ በሚያስደነግጥ ስፋትና ጥልቀት ተደራጅተው ስርአቱን እንደስርአት ለመናድ  የሚያስችል ህቡእ እንቅስቃሴያቸውን እንዲያጧጧፉ በማድረግ ረገድ የሕገጋዊነትን ሽፋን የሚያሰጣቸው አንዳንድ ወሳኝ የሚባል ስልጣን ያላቸው የክልል ወይም የፌደራል መንግስት አካላት አይምሩም ብሎ ማመን አያዳግምም ወይ? የሚለው ጉዳይም ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ሆኖ ነው የሚሰማኝ፡፡

አለበለዚያ ግን ዛሬ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለመደንገግ ያስገደዱንን እጅግ በጣም አሳሳቢ የሀገራዊ  ደህንነት አደጋዎች በሚጠበቀው ፍጥነት ቀለብሰን፣ የጋራ ሰላምና መረጋጋትን የመፍጠር   ጥረታችን ሁሉ አመርቂ ውጤት እንዳያመጣ የተለመደ እክል የመፈብረክ ደባቸውን ከመፈጸም ይቆጠባሉ ብሎ ማሰብ ተራ የዋህነት ከመሆን አያልፍም የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ ይልቁንም ደግሞ አ.ነ.ግ. በእንደዚህ አይነት ጀሌዎቹን አስርጎ የሚያስገባበትና የኢህአዴግ  መራሹን መንግስት ውስጣዊ ድከመቶች በውል ለይቶ ከማወቅ የሚመጭ ውዥንብር እያስነሳ  የኦሮሞ ወጣቶችን  የስርአቱ ጸር ሆነው እንዲቆሙ በማድረግ ረገድ የሚጫወተው አሉታዊ ሚና ምን ያህል ስር የሰደደ ልምድ እንዳለው የሚያመለክት ይመስለኝል፡፡

እንዲሁም ደግሞ በዶክተር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው ግንቦት 7 በተለይም አንዳንድ የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ተወላጅ የሆኑ ሰሊቃንን ሳይቀር ከትምክተኞቹ የተቃውሞው ጎሳ ፖለቲካ መሪ ተዋኒያን ጎን ተሰልፈው አልያም በህዝቡ ተመሳጥረው ፌደራላዊ ስርአቱን እንደስርአት ደርምስው እቺን ሀገር ደግሞ ወደ ቀድሞው አህዳዊ የመንግስት አወቃወት ለመመለስ ቆርጠው የተነሱት ጽንፈኛ ቡድኖች የሚያውጠነጥኑትን የቀለም አብዮት ለማቀጣጠል  ያለመ ደጋፍ እስከመስጠት እንዲደርሱ  የሚያደርገበት አግባብ መኖሩን ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ከዚህ የተነሳም በምእራቡ ዓለም የሚኖረው አክራሪ ዲያስፖራ ህብረተሰብና እንደነ ግንቦት ሰባት አይነቶቹ የግዛት አንድነትን ከመናፈቅ የሚመነጭ ትምክተኝነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ እሳቤን የሚያቀነቅኑ ቡድኖች የሚያስተባብሩትና የተቃውሞው ጉራን እንቅስቃሴ ወክለው እዚህ አገር ውስጥ ጉዳይ የማስፈጸም ጥረት ሲያደርጉ የሚያስተውሉት ወገኖች ‹‹አማራው በትምክተኝነት ስለተፈረጀና የኢህአዴግን የአፈና መዋቅር ትኩረት ሊስብ ስለሚችል የደቡቦቹ ወንድሞቻችን ከፊት ሆነው አደጋ የመቀነስ ሚና መጫወት ይገባቸዋል›› የሚል ፈሊጥ እንዳላቸው ይነገራል፡፡

ከዚህ አኳያ የሚታየውን የእምነት ማጉደል ተግባር እንዲፈጽሙ የአንድ አካባቢ ተወላጅነትን መሰረት ያደረገ ፈርጀ ብዙ ተጽእኖ የሚያደርስባቸውን የደቡብ ኢትዮጵያ ልሂቃንን በማሳመን ረገድ እንደዋነኛ ምክንያት የሚቀርበው አስነዋሪ አሉባልታ ደግሞ በተለይም ስርአቱ ‹‹ለትግሬዎቹ የበላይነት የቆመነው›› ከሚል አቅጣጫ የሚሰነዘረውና የጽንፈኛ ዲያስፖራ ተቃዋሚዎች ኢ.ምክንያታዊ መከራከሪያ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ለዚህ አይነቱ ጭፍን ድፍን ካለ የጥላቻ ፖለቲካ የሚመነጭ የአመለካከት እጅ ጥምዘዛ የመሪ ተዋናይነቱን ሚና ሲጫወቱ ከሚስተዋሉት የደቡባዊ ኢትዮጰያ ተወላጅ ምሁራን መካከል የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ ተብሎ የሚታመንባቸውም በተለይ እንደ አቶ አሰፋ ጫቦ እና  እንደ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ያሉት ዲያስፖራ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የእነርሱን መርዘኛ ፕሮፖጋንዳ ውጤት እንዲያመጣ አድርገው እዚህ አገር ውስጥ የመዛመትና የማስረጽ ተግባር እንዲያከናውኑ ሲባል እጅጉን በተጠና መልኩ የተደራጁ የደቡብ ክልል ተወላጅ ልሂቃን ስለመኖራቸውም ነው መረጃዎች የሚያመለክቱን ፡፡ እኔ በዚህ ረገድ ስለታዘብኩት ተጨባጭ  እውነታ ሳስብ ‹‹ወየው ለዚች አገር ህዝቦች ዘለቄታዊ እጣ ፈንታ›› የሚያሰኝ አስነዋሪና አሳፋሪም ጭምር የእብለት ተግባር መፈጸምን የተለየ እውቀት የሚጠይቅ ፖለቲካዊ ጥበብ አድርገው የሚቆጥሩ እሁራን ተብዬዎች የየአካባቢው ተወላጆች እንደ አሸን እየፈሉ መምጣታቸውን አምኜ እንድቀበል የሚገፋፋኝ ነው  ቢባል ጉዳዩን በተሻለ መልኩ የሚገልጸው ይመስለኛል፡፡

ወጣም ወረደ ግን የዚህ መጣጥፌ ግንባር ቀደም ማጠንጠኛ ስለሆነው የግብፃውያኑ ፖለቲከኞች፣ እንዲሁም ደግሞ ዲፕሎማቶች ሸፍጠኝነት የተጠናወተው አስተዛዛቢ ነገረ- ስራ ከላይ ለተት  የሞከርኩባቸውን አለም አቀፍ ታሪካዊ ደራን የሚያወሱ ነጥቦች በቅጡ ግንዛቤ ውስጥ እንዲገቡ የማድረግ ጉዳይ ከኢፌድሪ መንግስት ባለድርሻ አካላት እንደሚጠበቅ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡  

 ስለዚህ እንደኔ አረዳድ ከሆነ ከላይ ከተመለከትነው የግብጽ መንግስት አስተዛዛቢ ብሎም አስነዋሪ ጣልቃ ገብነት ጋር በተያያዘ መልኩ ስማቸው የተጠቀሰው ተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎች እየፈጽሙት ያለውን የሀገር ከሄደት ተግባር መላው ኢትዮጵያውያን ህዝቦች በአግባቡ ሊገነዘቡት ይገባል የሚል ጽኑ እምነት ነው ያለኝ፡፡

ለዚህ ጽሁ አቋሜ ወይም እምነቴ ምክንያታዊነት ደግሞ ሁለት መሰረታዊ የመከራከሪያ ነጥቦችን ማንሳት ብቻ በቂ ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪያው ነጥብ አሁን ሀገራችን ኢትዮጵያ ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት ይተገበራል ተብሎ የሚጠበቀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የሕገመንግስታችን አንቀጽ 93 በሚፈቅደወቅ መሰረት ለመደንገግ የተደነገገችበትን አሳሳቢ ችግር የጋረጡብን  ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለምምድነው በዚህ እጅግ ወሳኝ የታሪክ ምእራፍ የማይጠበቅ አይነት ሰው ሰራሽ እከላቸውን ከስር ከስር እየፈበረኩ የጋር ህልውናችንን ክፉኛ የሚፈታተን አደጋ ሊደቅኑብን የፈለጉት ? የሚለውን ጥያቄ በቅጡ የሚያበራራ ምላሽ ማቅረብ  የሚያሻው ሲሆን፣ሁለተኛው መሰረታዊ የመከራከሪያ ነጥብ ደግሞ፣ በተለይም የግብጽ ፖለቲከኞች ጉዳይ አስፈጻሚ የሆኑበት አግባብ ነው፡፡

ስለዚህ ሁለቱንም መሰረታዊ ነጥቦች አሳጥሬ በማብራራት የተጠቃሾቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች እቺን ሀገር እንደ ሀገር ለማተራመስ ያለመ ተግባር በእርግጥም ታሪክ ይቅር የማይለው ክህደት ስለመሆኑ ለማስረገጥ የሚቻልበትን አግባብ በማመላክት ሀሳቤን እቋጫለሁ፡

እንግዲህ ከዚህ ቀደም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፣ ሕገመንግስታዊ ስርአቱን ለመናድ ያለመ የአመጽ ተግባር ማውጠንጠንን  የመረጡት ጽንፈኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎች ዋነኛ ፍላጎት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው፣ በድህረ- ደርግ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን አዲስ የታሪክ ምእራፍ ተከትሎ መላው የዚች ሀገር ህዝቦች የተቀዳጇቸው ድሎች ይበልጥ ስር እየሰደዱ ሄደው የጨለማው ዘመን አሳፋሪ ገጽታዎችንን ሙሉ በሙሉ የሚቀይር ሁኔታ ሳይፈጠር  ሴራቸውን ለማሳካት እንደሆነ ነው፡፡   መላው የሀገራችን ህዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው ከድህነት ጋር የሞት ሽረት ትግል የገጠሙበት  ፈርጀ ብዙ የልማት ንቅናቄ ከጊዜ ወደ ጊዜ  እየጨመረ በመጣ ስፋትና ጥልቀት ይበልጥ ተጠናክሮ የመቀጣጠሉ ጉዳይ እጅጉን እንቅልፍ የሚነሳ ስጋት ስላሳደረባቸው የመጨረሻውን የሞራል ዝቅጠት በሚጠይቅ አስነዋሪ ፖለቲካዊ ደባ የአንዱን ብሔር ብሔርሰብ ህዝብ ከሌላኛው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ደም የሚቃባበት ሙከራቸውን አጥብቀው ተያያዙት፡፡

በተለይም ደግሞ ያለፈው  2007 ዓ.ም ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ፈርጀ ብዙ የህዳሴ ጉዞ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ ጎለቶ እንዲጸባረቅ ያደረጉና የአለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት ጨምር የሳቡ ታላቅ የዲፕሎማሲያዊ ድሎች ያስመዘገቡት ስኬታማ የበጀት አመት እንደነበር ሲታወስ ጉዳዩ ጽንፈኞቹን ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ወደለየለት የእብደት ተግባር ሳይመራቸው እንዳልቀረ መገመት አይከብድም፡፡ ይልቁኑም ደግሞ የበለጽጉትን ምእራባውያን ሀገራት ጨምሮ መላውን የዘአመናች አለም በሃይማኖት ሽፋን የሚንቀሳቀስ ጽንፈኛ  የፖለቲካ ቡድኖች ለሚፈጽሙት ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት እየተደረገ ማጣፊያው አጥሮት በሚስተዋልበት ቀውጢ ወቅት የኛዋ ሀገር ኢዮጵያ አስተማማኝ ሰላም መረጋጋቷን አስጠብቃ የመገኘቷ ጉዳይ የቀለም አብዮት ናፋዊዎቹን ሃይሎች ፈጽሞ እረፍት የሚነሳ ራስ ምታት  እንደሆነባቸው ነው በርካታ ዜጎቻችን ከሚሰጡት ነፃ አስተያየት መረዳት የሚቻለው፡፡

እናም የዛሬዋ ኢትዮጵያ ምልአተ ህዝቦች እንደ አንድ ህብረተሰብ በመላው አለም አቀፍ ህብረተሰብ ዘንድ አድናቆትና ከበሬታን ያተረፍንባቸው የህዳሴው ዘመን በጎ ገጽታዎችን ሁሉ ምቾት አልሰጥ ያሏቸው የትምክህት እና  የጠባብ ብሄርተኝነት ጽንፈኛ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ አቀንቃኞቹ ተቃዋሚ ቡድኖች ከየትኛውም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ጋር ወግነው እጂን እቺን ሀገር በአመፃ ተግባር ማተራመስ እንዳለባቸው ማመናቸውን  የሚያረጋግጥ ድርጊት ሲፈጽሙ የታዘብንበት ነው የ2008 ዓ.ም ተደጋጋሚ ሁከትና  ግርግር፡፡

ስለዚሀም በእኔ እምነት የአፍሪካ የውሃ ማማ ስለመሆኗ መላው አለም የመሰከረላት ሀገር ህዝቦች ሆነን ሳለ‹‹ የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው›› ወዘተ…… በሚል ተረትና ምሳሌ ከመቆዘም ያለፈ እጣ ፈንታ የማይኖረን መስሎ እስኪሰማን ድረስ ለዘመናት ያህል በዘለቀ ቁጭት ስንገበገብ ከቆየን በኋላ የጀመርነውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ሂደት ለማስቆምና የጋራ ብሩህ ተስፋዎቻችንን ለማጨለም ከሚፈልጉ እንደ ግብጽ ያሉ ሀገራት ጋር ተመሳጥረው በጉዳይ አስፈፃሚነት ሲንቀሳቀሱ የሚስተዋሉት ተቃዋሚዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ለትኛውንም የብሔር ብሔረሰብ ህዝብ መብትና ጥቅም እንታገላለን ብለው ለመናገር የሚያስችል የሞራል ብቃት ያላቸውም ባይ ነኝ፡፡ ይህን ጽኑ አቋም እንድይዝ ከሚያስገድዱኝ መሰረታዊ ምክንያቶች እንደዋነኛ የምወስደው ነጥብም ደግሞ ፣በተለይም ሀገራችን በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብን ሰርተን ትርጉም ላለው ኢኮኖሚያዊ የጋራ ጥቅም ስለማዋል ጉዳይ እንደህብረተሰብ የተስማማንበት አግባብ ተግባራዊ እንዳይደረግ ማንኛውንም አይነት እክል በመፍጠር የሚገልጽ የተቃውሞ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ሁሉ በምንም መልኩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክል ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም  የሚለው ይናል ነው ፡፡

ስለዚህ መላውን የኦሮሞ ህዝብ ጨምሮ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለእለት ጉርሱ ለዓመት ልብሱ ከሚያውላት የገቢ ምንጩ ላይ እየቀነሰ በሚያወጣው ገንዘብ አማካኝነት የግንባታ ሂደቱ እየፋጠነ የሚገኘውን የታላቁን የህዳሴ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨ ግድባችንን ለማስቆም ያለመ የእክል ፈጠራ ሴራቸውን ከማውጠንጠን ካልቦዘኑት የግብጽ መንግስት ሸፍጠኛ ዲፕሎማቶች ጋር እየተመሳጠሩ እችን ሀገር ለማተራመስ ሲባል የሚቃጣብንን ተደጋጋሚ የአመጽ ተግባር ከማቀነባበር  እስከ መሞከር የሚደርስ ጉዳይ አስፈፃሚነትን እንደ የትግል ስልት የቆጡት ኦ.ነ.ግ እና መሰሎቹ የለየላቸው ከሀዲዎች ተደርገው ይወሰዱ ዘንድ ተገቢነቱ አይጠየቅም፡፡

በዚህ ረገድ እንኳንስ ሰፊው የኦሮሚያ ክልል ህዘብ ሌላ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የህብረተሰብ ክፍልም ቢሆን ብዥታ  ይኖርበታል ተብሎ እንደማይታመንና  የነገ መፃኢተስፋውን ያለመለመለትን  የዚችን አገር የህዳሴው ጉዞ ለቅልበሳ አደጋ በሚያጋልጥ የቀለም አብዮተኞች የትርምስ እስትራቴጂ ለሚመጣ የስርአት ለውጥ ከውጭ ሃይሎች ጋር የሚደረግን ድርድር እንደማይቀበል ጭምር ያለኝን ጽኑ እምነት ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

ስለዚህ ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ያላቸውን የውጭ ሃይኖች የሚያቀነባብሩትን መሰል የሁከትና ግርግር ተልእኮ ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ የሚስተዋሉት ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች ሁሉ በራስ ሀገር ወገን ላይ ታሪክ ይቅር ሊለው የማይችል ክህደት ተግባር እየፈጸሙ የመሆናቸው ጉዳይ ሊሰበርበት እንደሚገባው ነው  የሚሰማኝ ለኔ፡፡  በተረፈ ግን ኢትዮጵያውያን ህዝቦችን ‹‹ የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው›› ወዘተ…. ወደተሰኘ ቁጭት አዝልቆ ቁዘማችን መልሰው ለመውሰድና ያው እንደተለመደው ሁሉ በናይል ተፋሰስ  ጉዳይ የበይ ተመልካች ሆነን እንድንቀርብላቸው ለማድረግ የሚፈልጉት ግብፃውያን የፖለቲካ ልሂቃን አሁንም ድረስ ከመጋረጃቸው በስረጀርባ እየተመሰጣሩ በሀገራችን ላይ የሚዶልቱትን የጥፋት ሴራ ያቆሙ ዘንድ የሚያስገድድ ዲፕሎማሲያዊ ተጽእኖ በመፍጠር ረገድ የኢፌድሪ መንግስትከ ጊዜ ይልቅ ጥረት ማድረግን የሚጠይቅ የቤት ስራ መስራት እንደሚጠበቅበት አያከራክርም፡፡

አለበለዚያ ግን ከላይ ለመጠቆም በተሞከሩት መሰረታዊ ነጥቦች ምክንያት ወደለየለት ተስፋ መቁረጥና ቅን አስተሳሰብን ገድሎ ወደ ሚቀብር የሞራል ዝቅጠት እየወረዱ የመጡት ጽንደኞች ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች አሁን አሁን የሚያሳዩት አደገኛ አዝማሚያ እንኳንስ እንደነርሱ የሰው ስጋ ለብሶ ከተፈጠረ ፀረ -ኢትዮጵያዊ ውጭ ሃይል፣ ከሰይጣን አለቃ ከሳጥናኤል ጋርም ቢሆን ተሻርከው እቺን ሀገር የማተራመስ አጀንዳቸውን ለማበርከት መሞከራቸው እንደማይቀር ከወዲሁ መገንዘብ  አይከብድም፡፡ እናም የጉዳዩ አሳሳቢነት ከዚህ አኳያ ተጢኖ የተጋረጡብንን  የሀገራዊ ደህንነት አደጋዎች ሁሉ በቅጡ ለመመልከትና እንዲሁም ደግሞ በማያዳግም መልኩ ለማምከን የሚያስችል ዘለቄታዊ የመፍትሔ አቅጣጫ መቀየስ እንደሚገባ ነው እኔ በግሌ ላስገነዝብ የምሻው፡፡ መቸስ አሁን ከገጠመን ፈተና ብዙ የምንማረው ቁም ነገር እንዳለና ተመሳሳይ ችግሮችን የሚጋብዙ ስህተቶች እንደሚታረሙ ተስፋ አሰርጋለሁ፡፡ መአ ሰላማት  !