49 የሞጆ ደረቅ ወደብ ማሽኖች ርክክብ ተደረገ

የወደብ አገልግሎትን ለማቀላጠፍ የሚያግዙ 49 የወደብ የተለያዩ ማሽኖች ግዢ ተፈፅሞ በሞጆ ደረቅ ወደብ ርክክብ ተከናውኗል።

የማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን የሚመራው ሎጅስቲክስ ማዕከል የሞጆ ሎጅስቲክስ ማዕከል ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ ከሀምሌ 2009 ዓ.ም ጀምሮ በመተግበር ይገኛል።

የዚሁ ፕሮጀክት አካል የሆነውና የሞጆ ደረቅ ወደብ አቅምን ለመገንባትና ለማዘምን የሚያስችሉ 49 የወደብ ማሽኖች ግዢ ተፈፅሞ ርክክብ ተደርጓል።

ማሽኖቹ ከዓለም ባንክ በተገኘ 19 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር ብድር ግዢው የተፈፀመ ሲሆን የፕሮጀክቱን 13 በመቶ ይሸፍናልም ተብሏል።

የትራንስፖርት ሚንስትሯ ዳግማዊት ሞገስ፣ የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ ፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ እንዲሁም ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የርክክብ ስነስርዓት ተከናውኗል።

የትራንስፖርት ሚንስትሯ ዳግማዊት ሞገስ በርክክቡ ወቅት እንዳሉት የተቋሙን የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ለማሳካት የደረቅ ወደብን አገልግሎት ቀልጣፋና ዘመናዊ ማድረግ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።

ማሽኖችም ጊዜን በመቆጠብ አግልግሎቱን በማዘመንና ወጪን ይቀንሳሉ ብለዋል።

የማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ በበኩላቸው በሁለተኛ ዙርም በተለይ በወደቡንና በባቡር መካከል ያለውን ምልልስ ለማቀላጠፍ የሚያስችሉ የ25 ማሽኖች ግዢ እየተከናወነ መሆኑን ተናርዋል፡፡

የሞጆ ወደብ ሎጅስቲክስ ማዕከል ሲጠናቀቅ የወጪና ገቢን ንግድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳረ የሚያደርግ ሲሆን የወደብ ማሽኖቹ ከከፍተኛ እስከ መለስተኛ ጭነቶችን ለማከናወን ያስችላሉ ተብሏል።

(በትዕግስት ዘላለም)