500 የብልፅግና ፓርቲ ሴት ሊግ አመራሮችና አባላት ደም ለገሱ

መጋቢት 23/2013 (ዋልታ) – 500 የብልፅግና ፓርቲ ሴት ሊግ አመራሮችና አባላት ደም ለግሰዋል።

የደም ልገሳው የተካሄደው ”ደማችን ለወገናችን እየሰጠን ድምፃችንን ለብልፅግና ፓርቲ እንሰጣለን!” በሚል መሪ ሃሳብ ነው፡፡

የሊጉ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ መላኬ ዓለማየሁ እንደገለጹት፤ የደም ልገሳው በደም እጦት ህይወታቸውን ለሚያጡ ወገኖች ለመድረስ ነው።

በአገሪቱ የተከሰተው የደም እጥረት በተለይም የኦ የደም አይነት እጥረት በመኖሩ ለልገሳው እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል፡፡

ልገሳውን ካደረጉት መካከል ወይዘሮ ሃና አበበ፤ “ለወገን ደራሽ ወገን ነውና ደማችንን ለወገኖቻችን አበርክተናል” ብለዋል።

ደም መለገስ በማንኛውም ጤነኛ ግለሰብ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ባለመኖሩ ሁሉም ለወገኑ ሊደርስ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከኢዜአ የተገኘው መረጃ እንዳመላተው ከለጋሾቹ መካከል ወይዘሮ ብፅአት ተስፋዬ፤ “ደሜን ለወገኔ በማድረሴ ደስተኛ ሆኛለሁ” ብለዋል።