554 ኢትዮጵያዊያን ከተለያዩ ሀገራት ተመለሱ

ሚያዚያ 08/2013 (ዋልታ) – 554 ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ከተለያዩ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

339 ኢትዮጵያዊያን ከሳዑዲ አረቢያ ሪያድ ከተማ የተመለሱ ሲሆን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ተወካይ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ተገኝተው ለተመላሾቹ አቀባበል አድርገዉላቸዋል።

በተመሳሳይ በቤይሩት  ህጋዊ   ሰነድ የሌላቸውና  በችግር  ውስጥ የነበሩ ዜጎች፤ ያለቅጣት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ  በቤይሩት የሚገኘው የኢትዮጵያ  ቆንስላ ጽህፈት ቤት  ከሀገሪቱ መንግስት ጋር መግባባት ላይ መድረሱን ተከትሎ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ከቤይሩት ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡

በዚህ መሰረት በታህሳስ ወር በ2013 ዓ.ም   ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ተመዝግበው  ከነበሩ አንድ ሺህ 239 ዜጎች መካከል  ከሚያዚያ አምስት እስከ ሰባት  2013 ዓ.ም  ድረስ 215 የኢትዮጵያ ዜጎች ከሊባኖስ ከተማ ወደ ሀገራቸው መግባታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡