6ኛው ሀገራዊ ምርጫን ሰላማዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

መጋቢት 09/2013 (ዋልታ) – 6ኛው ሀገራዊ ምርጫን ሰላማዊ ለማድረግ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሀገሪቷ ባወጣቻቸው ህጎችና በህገ መንግስቱ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ባከበረ መንገድ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ እና ሀገራዊ የጸጥታ ሁኔታን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የኮሚሽኑ የወንጀል ወከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ እና የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴ ናቸው።

የፌደራል ፖሊስ ያለፉት አምስት ምርጫዎች የነበሩት የምርጫ ተግባራትን ገምግሟል፡፡

በዚህም አንዳንድ የፖሊስ አመራሮች  የፓርቲ አባል ሆነው የፓርቲ አጀንዳ የሚያራምዱ እንደነበሩ አስታውቋል፡፡

ጠንካራ የነበሩ የምርጫ ማስፈጸም ስራዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል ሙሉ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ኃላፊዎቹ ተናግረዋል።

በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የፌደራል ፖሊስ በገለልተኝነት እና በህግ መሰረት ምርጫውን ለማስፈጸም አቅጣጫ መቀመጡ ነው የተገለጸው፡፡

የምርጫውን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ ከሚሰራው ስራ ጎን ለጎን የምርጫ ጉዳይን ብቻ የሚመለከት የምርመራ ክፍል በማቋቋም አደረጃጀቱም እስከ ዞን ድረስ እንደሚወርድ በመግለጫው ተጠቅሷል።

በፖሊስ የምርጫ ዝግጅት የተመራጮች ምዝገባ በሰላማዊ መንገድ ማካሄድ የመራጮች ምዝገባና የምርጫ ቁሳቁስ ማድረስ ስራ ያለምንም ችግር ለማከናወን ዝግጅት መደረጉ ተገልጿል።

ምርጫውን በማጭበርበር ወይም የምርጫ ኮረጆ ገልብጦ የትኛውም ኃይል ወደ ስልጣን አይመጣም ለዚህም ሙሉ ዝግጅት ተደርጓል ተብሏል፡፡

የፖሊስ የምርጫ ማስፈጸም እቅድ መውጣቱ እና መመሪያም መዘጋጀቱም ነው የተገለጸው፡፡

(በምንይሉ ደስይበለው)