6ኛው ሀገራዊ ምርጫን ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ብልጽግና ፓርቲ ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገለጸ

የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዐቢይ አህመድ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 08/2013 (ዋልታ) – ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ብልጽግና ፓርቲ ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር በትብብር እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ በምርጫ ወቅት የሚጠቀምበትን ማኒፌስቶና የምርጫ መወዳደሪያ ምልክትን በዛሬው ዕለት ይፋ አድርገዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዐቢይ አህመድ፣ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የሚያሸንፉበት እንደሚሆን ገልጸው፣ ብልጽግና ፓርቲ የጀመረውን ውጥን አሳክቶ የሚያሳይ መሆኑን ያለፉት አመታት ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መጻኢ እድልና ተስፋ ብርሃን መሆኑን ለማመላከት የመወዳደሪያ ምልክቱ እየበራ ያለ አምፖል መሆኑን ያሳወቀው የብልጽግና ፓርቲ፣ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ለመወዳደር የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ፓርቲው የመወዳደሪያ ምልክቱን እየበራ ያለ አምፖል ያደረገበት ምክንያት ኢትዮጵያውያን ብርሃንን ተከትለው ወደ ብልጽግና መጓዝ እንዲችሉ እንዲሁም ህብረትን እና ውበትን ለማመላከት መሆኑ ተገልጿል፡፡

ፓርቲው ከዚህ በፊት የነበረውን ወይንም የአሁኑን ብቻ የሚያይ ሳይሆን ወደፊት የሚመጣውን ብሩህ ተስፋ አመላካች ነውም ተብሏል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ያለፉትን ጊዜያት በርካታ ችግሮች በጽናት በማለፍ በርካታ ስራዎች ሰርቶ ማሳየት የቻለ ፓርቲ መሆኑን የገለጹት የብልጽግና ፓርቲ የጽህፈት ቤት ኃላፊ ብናልፍ አንዷአለም ፓርቲው ለነገ ብሩህ ተስፋ ዛሬ ላይ ራዕይ ሰንቆ የሚሰራ ነው ብለዋል፡፡

በኢኮኖሚ ራሷን የቻለች ሀገር ለመገንባት በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና ሌሎች ዘርፎችም የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ፓርቲው በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡

(በሜሮን መስፍን)