6ኛ ዙር ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ በተለያዩ ክልሎች እየተካሄደ ነው

ሰኔ 16/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌ እና በማዕከላዊ የኢትዮጵያ ክልሎች በዛሬው ዕለት 6ኛውን ዙር ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ እያካሄደ ነው፡፡

በየምርጫ ጣቢያዎች የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከመለዳ 12 ሰዓት ጀምሮ ድምጹን እየሰጡ ይገኛል።

በዚህም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መስቃን ማረቆ በሚገኙ 169 የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ሂደቱ ተጀምሯል።

በሶማሌ ክልል 6ኛው ዙር ቀሪና የድጋሚ ምርጫ በ123 የምርጫ ጣቢያዎች እየተካሄደ ይገኛል።

በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች ተደርገው በክልሉ ጅግጅጋ ከተማ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ይወዳደራሉ ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ ሁለት የግል ተወዳዳሪዎች በምርጫው ይሳተፋሉ ነው የተባለው።

በአፋር ክልል ጋዋኔ ወረዳ በሚገኙ 45 የምርጫ ጣቢያዎች ለክልልና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ለሚወዳደሩ ዕጩዎች ህዝቡ ድምጹን እየሰጠ ይገኛል።

በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ከተማ 6ኛው ዙር ሀገራዊ ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ በመካሔድ ላይ ይገኛል።

በሔኖክ ለሜ፣ ሳራ ስዩም፣ ግዛቸው ግርማዬ እና ሚልኪያስ አዱኛ