ጳጉሜ 02/2013 (ዋልታ) መንግስት የኑሮ ውድነትና የኢኮኖሚ አሻጥርን ለመቀነስ የምግብ ዘይት አቅርቦትና ስርጭትን ለማሳደግ 62 ሚሊየን ሊትር ጥራቱን የጠበቀ የምግብ ዘይት ለገበያ ዝግጁ ማድረጉን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የምግብ ዘይት አቅርቦትና ስርጭት ችግሮችን ለመቅረፍ ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ የምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች አቅርቦቱን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን በሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክትር ወ/ሮ አበባ ታመነ ገልፀዋል፡፡
በዚህም 36.5 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት ከውጪ እየገባ ሲሆን፣ ቀሪው 25.5 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት በሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚሸፈን መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም በኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢ ድርጅት እና በሌሎች የገባው የምግብ ዘይትም ባለ ሁለት፣ ሶስት እና እምስት ሊትር ሲሆን፣ 50 በመቶ የሚሸፍነው ባለ አምስት ሊትር የምግብ ዘይት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
የገባው ዘይት በቀጥታ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በሸማች ማህበራት በኩል በዛሬው ዕለት ከሰዓት በኋላ እና በነገው ዕለት እንደሚሰራጭ በመግለጽ፣ በቀጣይ በባቡር የሚገባ ስለሆነ የአቅርቦት ችግር እንደማይኖር መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡