በህገ-ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 16 ኪሎግራም ወርቅ ተያዘ

ግንቦት 1/2014 (ዋልታ) 64 ሚሊዮን ብር የሚገመት ወርቅ በህገ-ወጥ መንገድ ደብቆ ኬላ ጥሶ ለማለፍ የሞከረው አሽከርካሪ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ የጉምሩክ እና በአካባቢው በነበሩ የኦሮሚያ ክልል የሚሊሻ ኃይል ባደረጉት ብርቱ ክትትል በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ፖሊስ ገለፀ።

ሚያዝያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ በ11:30 በኦሮሚያ ክልል ነጌሌ ቦረና ከተማ ዶሎ በር ኬላ ትዮታ ደብል ፒክአፕ ላንድ ክሩዘር ከነጋሌ ከተማ ወደ ሶማሌ ክልል ለመሄድ ቀጥታ በጉምሩክ ኬላ በኩል መጥቶ ለፍተሻ ሲያስቆሙት ፊቃደኛ ባለመሆን በኬላው ጎን ባለው የእግረኛ መንገድ በመጠቀም ጥሶ ለማለፍ ሲሞክር ለማስቆም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት ጥይት ቢተኩሱም ሳይቆም በማምለጥ ላይ እያለ ነው በቁጥጥር ስር የዋለው፡፡

በዞህም የጉምሩክና የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት በአካባቢው ለነበረው ኮማንድ ፖስት መረጃውን በፍጥነት በማስተላለፍ ዶሎ በር አካባቢ በሚገኘው የእርዳታ እህል ማራገፊያ አየር ማረፊያ አካባቢ የኦሮሚያ የሚሊሻ ኃይል ባደረጉት ብርቱ ክትትል ተሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ውሏል።

በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት ሲፈተሽም 16 ኪ.ግ ወርቅ የተገኘ ሲሆን አሁን በገበያ ላይ ባለው ዋጋ በብር ሲተመን 64 ማሊየን ብር የሚያወጣ መሆኑ ተረጋግጧል።

ከነአሽከርካሪው በቁጥጥር ስር የዋለው ወርቅም በኦሮሚያ ክልል ነጌሌ ከተማ በሚገኘው የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ መጋዘን ገቢ እንደተደረገ የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል።

 

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!