ሃምሌ 03/2013 (ዋልታ) – በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለ692 የፌደራል ታራሚዎች ይቅርታ መደረጉን የይቅርታና ምህረት ቦርድ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በበጀት ዓመቱ ለአንድ ሺህ 307 ታራሚዎች ይቅርታ እንዲደረግ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን የቦርድ ጽህፈት ቤቱ ከህግና ማስረጃ አንፃር ጥያቄዎቹን በመመርመር ለቦርድ አቅርቦ ቦርዱም በይቅርታ አሰጣጥና አፈፃፀም ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 840/2006 መሰረት የህዝብ፣ የመንግስትና የታራሚዎችን ጥቅም ከግምት በማስገባት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
የይቅርታ እና ምህረት ቦርድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዘለቀ ዳለሎ በተገባደደው በጀት ዓመት ይቅርታ ሊደረግላቸው ይገባል ተብለው የተለዩ የፌደራል ታራሚዎች ማስረጃ ለቦርዱ የቀረበ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ይቅርታ ከተደረገላቸው ታራሚዎች ውስጥ 48 ከእስራት ፍርድ በተጨማሪ የገንዘብ መቀጮ እንዲከፍሉ በፍርድ ቤት በመወሰኑ የተጣለባቸዉን የ487 ሺህ 800 ብር ቅጣት እንዲከፍሉ የማድረግ ሥራ መሰራቱን ከኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡
ማስረጃዎችን ትክክለኝነት ማረጋገጥ በሚቻልባቸውና መወሰድ ባለባቸው የመፍትሄ አቅጣጫዎች ዙሪያ ጥናት በማካሄድና በማጽደቅ ግልጽ የሆነ የአሰራ ሥርዓት በመዘርጋት ሥራ መጀመሩን አስታውቋል፡፡