ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከታሊባን ጋር የነበረውን የሰላም ስምምነት መሰረዛቸውን አስታወቁ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከታሊባን ጋር የነበረውን የሰላም ስምምነት መሰረዛቸውን አስታወቁ።

ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ የአፍጋኒስታኑን ፕሬዝዳንት አሽራፍ ጋህኒ እና የታሊባን መሪዎችን ለማግኘት ቀጠሮ ይዘው እንደነበር አስታውቀዋል።

ይሁን እንጂ ሐሙስ ዕለት በአፍጋኒስታን መዲና ካቡል በተፈጸመው እና ታሊባን ኃላፊነቱን በወሰደው ጥቃት አንድ የአሜሪካ ወታደር መገደሉን ተከትሎ ትራምፕ የሰላም ስምምነቱን ሰርዘዋል።

ሁለቱ አካላት ከሰላም ስምምነት እንዲደርሱ የአሜሪካ መንግሥት እና የታሊባን ተወካዮች በኳታር ዶሃ ከዘጠኝ ጊዜ በላይ ተገናኝተው መክረዋል። የሰላም ስምምነቱ አደራዳሪዎች ከቀናት በፊት አሜሪካ እና ታሊባን ‘በመርህ ደረጃ’ ከሰላም ስምምነት ደርሰዋል ብለው ነበር።

ታሊባን ፈጽሜዋለሁ ባለው ጥቃት አንድ የአሜሪካ ወታደር ከተገደለ በኋላ፤ ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ “በአስቸኳይ ውይይቶቹ እና የሰላም ድርድሩ እንዲቆም አዝዣለሁ” ብለዋል።

የሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚ ቢሆን ኖሮ አሜሪካ ወደ አፍጋኒስታን ካዘመተቻቸው ወታደሮች መካከል 5400 የሚሆኑት በ20 ሳምንታት ውስጥ ልታስወጣ ነበር።

በአሁኑ ሰዓት አሜሪካ በአፍጋኒስታን ከ14 ሺህ በላይ ወታደሮች አሏት። ሐሙስ ዕለት በካቡል መኪና ላይ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ አሜሪካዊውን ወታደር ጨምሮ 12 ሰዎች ተገድለዋል።

ታሊባን በምፈጽማቸው ጥቃቶች ዒላማ የማደርገው የውጪ ሀገር ኃይሎችን ነው ይበል እንጂ በጥቃቶቹ ለከፍተኛ ጉዳት የሚዳረጉት ንጹሐን የአፍጋኒስታን ዜጎች ናቸው።

አሜሪካ እ.አ.አ. 2001 ላይ አፍጋኒስታንን ከወረረች ወዲህ ከ3500 በላይ የውጪ ሀገራት ጥምር ኃይሎች ተገድለዋል። ከእነዚህም መካከል 2300 የሚሆኑት አሜሪካውያን ናቸው።

ባለፉት 18 ዓመታት ምን ያክል የአፍጋኒስታን ሲቪሎች፣ የመንግሥት ወታደሮች እና ታጣቂ ሚሊሻዎች ህይወታቸውን እንዳጡ በውል አይታወቅም።

ከወራት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው ሪፖርት መሰረት ከ32 ሺህ በላይ ሲቪሎች የተገደሉ ሲሆን፣ ሌሎች ተቋማት በበኩላቸው የውጪ ኃይሎችን ሲፋለሙ የነበሩ ከ42 ሺህ በላይ ሚሊሻዎች መገደላቸውን ይጠቁማሉ። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)