ብራዚል የአማዞን እሳትን ለማጥፋት ወታደር ልትልክ ነው

የብራዚል ፕሬዘዳንት ጃዬር ቦልሶናሮ፤ በአማዞን ደን የተነሳውን እሳት ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት የአገሪቱ ወታደራዊ ኃይል ድጋፍ እንዲሰጥ ትዕዛዝ አስተላለፉ።

በፕሬዘዳንቱ ውሳኔ መሰረት በጥብቅ ተፈጥሯዊ ሥፍራና በድንበር አካባቢ ወታደሮች ይሰማራሉ። ውሳኔው ይፋ ከመደረጉ አስቀድሞ የአውሮፓ መሪዎች ብራዚል ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረጉ ነበር።

“ወታደር እንደመሆኔ የአማዞን ጫካን እወደዋለሁ፤ ልታደገውም እፈልጋለሁ” ሲሉ ፕሬዘዳንቱ ንግግር አድርገዋል።

ወታደሮቹ ይሠማራሉ የተባለው ለአንድ ወር ሲሆን፤ የመከላከያ ሚኒስትሩ ፈርናንዶ አዜቬዶ ኤ ሲልቫ ሂደቱን ያስፈጽማሉ ተብሏል።

ብራዚል በአማዞን ጫካ የተከሰተውን እሳት ለማጥፋት ያላሰለሰ ጥረት ካላደረገች ፈረንሳይና አየርላንድ ከሰሜን አሜሪካ ጋር ሊያደርጉት የነበረውን የንግድ ስምምነት እንደማያጸድቁ ተናግረዋል።

የብራዚል ፕሬዘዳንት በበኩላቸው መሪዎቹ “በአማዞን ደን የተነሳውን እሳት አስታከው ማዕቀብ መጣል አይችሉም” ሲሉ ተችተዋል።

በአሁን ወቅት የአውሮፓ ሕብረት ካውንስል መሪ የሆነችው ፊንላንድ የገንዘብ ሚኒስትር፤ የአውሮፓ ሕብረት የብራዚል የሥጋ ምርት ላይ ማዕቀብ እንዲጥል ጠይቀዋል።

የተፈጥሮ ጥበቃ ላይ የሚሠሩ ቡድኖች ባሳለፍነው አርብ በመላው ብራዚል ሰላማዊ ሰልፍ አድርገው ነበር። በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ብራዚላዊያንም ተቃውሟቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።

የዓለም ግዙፉ ደን እንዲሁም “የዓለም ሳምባ” እየተባለ የሚሞካሸው አማዞን የሙቀት መጠን መጨመር ጋብ እንዲል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

አማዞን የአንድ ሚሊየን ሰዎች መኖሪያ ከመሆኑ በተጨማሪ ከሦስት ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ እጽዋትና እንስሳት መገኛም ነው።

የጀመርኗ መራሔተ መንግሥት አንግላ መርኬል፣ የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን እሳቱን “ዓለም አቀፍ ቀውስ” ብለውታል።

አንግላ እና ኢማኑኤል በ ጂ-7 ውይይት ላይ የአማዞን ደን እሳት ለውይይት መቅረብ እንዳለበትም ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ በትዊት ገጻቸው ላይ “ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ውስጥ በምትገኝበት በዚህ ወቅት፤ ቀዳሚ የኦክስጅን ምንጫችን የሆነው የአማዞን ደን አደጋ ውስጥ መውደቅ አይገባውም” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።