72ኛው የአውሮፓ ቀን ግንቦት 1 ይከበራል

ሚያዝያ 26/2014 (ዋልታ) 72ኛው የአውሮፓ ቀን ግንቦት 1 እንደሚከበር ተገለጸ፡፡
መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ በአፍሪካ ኅብረት የአውሮፓ ኅብረት ዲፕሎማቶች ቀኑን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከበቃ 5 ዓመታት በኋላ የተመሰረተው የአውሮፓ ኅብረት ባለፉት ሰባት አስርት ዓመታት 27ቱ የአውሮፓ ሀገራት የፖለቲካ የፀጥታ የኢኮኖሚ ውህደት በማምጣት ከፍተኛ ውጤት አምጥቷል ተብሏል።
በኢትዩጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮብያ ኢትዮጵያና አውሮፓ ኅብረት ከ40 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ታሪካዊ የሚባል የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት ባላቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከሁለትዮሽ ባለፈ ዓለም ዐቀፍ ጉዳዩች ላይም አብረው ይሰራሉ ያሉት አምባሳደሩ ከኅብረቱ ጋር ብቻ ሳይሆን ከኅብረቱ አባል ሀገራት ጋርም ቢሆን ጠንካራ ግንኙነት አላት ብለዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር 2ኛው የንግድ ልውውጥ ያላቸው ናቸው ያሉት አምባሳደር ሮላንድ ኮብያ ይህም ኢቢኤ (EBA) ወይም ነፃ የገበያ መዳረሻ ከጦር መሳሪያ ውጭ በሚል ከታክስ ነፃ እቃዎችን ወደ አውሮፓ እንዲገቡ በማድረግ ተጠቃሚ እየሆነች ነው ብለዋል።
በአፍሪካ ኅብረት የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ጂፖ በበኩላቸው አፍሪካና የአውሮፓ ኅብረት ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሲሆኑ ከየትኛውም አኅጉር በፊት የአውሮፓ ኅብረት የመጀመሪያውን ኤንባሲ የከፈተው አፍሪካ ላይ አዲስ አበባ ነው ብለዋል።
በንግድ፣ በሰላምና በልማት ጉዳዮች አብረው ይሰራሉ ያሉት አምባሳደሩ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ የንግድ ልውውጡ እና በልማት መስኮች ከፍተኛ የሆነ ትብብር እንዳላቸውና በንግድ ልውውጥም ቢሆን ከየትኛውም ሀገር በበለጠ የአውሮፓ ኅብረት ከአፍሪካ ኅብረት ሀገራት ጋር የሚያደርገው የመጀመሪያውን የሚይዝ ነው ሲሉም ነው ያብራሩት።
72 ኛው የአውሮፓ ቀን በፊልም ፌስቲቫልና በህጻናት ሩጫ ይከበራል ተብሏል።
በምንይሉ ደስይበለው