የሀይማኖት አባቶች ለዘመን መለወጫ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላ

የ2012 የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የሀይማኖት አባቶች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

አዲስ የዘመን መለወጫ  ተብሎ የሚነገርለት ዕለት አዲስ ሊሆን የሚችለው በዋናነት ልቦና ሲታደስ ነው ያሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁእ አቡነ ማትያስ፤ በአስተሳሰብ፣ በስራና በአኗኗር ሁሉ ከልብ የሆነ መታደስ ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል፡፡

“የኢትዮጵያን ህዳሴን እናበስራለን” የሚለው መልካም ምኞት ከቃላት ባለፈ  በይቅርታና እውነተኛ መግባባት በሁሉም ወገኖች መከናወን እንዳለበት በመጥቀስ፤ በሃሳብ መቀራረብና በሰጥቶ መቀበል መርህ እየተቻቻሉ መሄድን እንደአዋጭ ባህል አድርገን መጓዝ ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ይህ ታላቅና ባለታሪክ ህዝብ ለዘመናት ተንከባክቦ ያቆየው ሃይማኖቱን፣ ታሪኩን፣ ባህሉንና አንድነቱን አሁንም ፣ነገም ሆነ ከነገ በኋላ ጠብቆ እንዲጓዝ መሰናክል አናብዛ ያሉት ብፁዕነታቸው፤ ይህን በማድረግ በእግዚአብሄርና በታሪክ ፊት በደል ከመፈፀም እንጠንቀቅ ብለዋል፡፡

አዲሱ ዓመት የሰላም ፣ የፍቅር ፣ የአንድነት፣ የስምምነትና የይቅርታ ዘመን ማድረግ የምንችለው ከእግዚአብሄር በታች እኛው በመሆናችን ልዩነቶችን ወደ መቀራረብ ብሎም ወደ ፍፁም  መተማመን በማምጣት ሀገሪቱንና ህዝቦቿን ወደ ላቀ ህዳሴ  እናሸጋግር ሲሉ አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በአዲሱ 2012 ዓመት መልካም ነገርን ለማቀድና ለመስራት ልባችንን ከፍተን በፍቅር፣ በይቅርታ፣ በአንድነትና በህብረት መንፈስ ልንጀምረው ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀዻዻሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ናቸው፡፡