መስከረም 4/2015 (ዋልታ) በአየር ንብረት ለውጥ እና ሌሎች የዓለም አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው 77ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ በኒው ዮርክ ዛሬ ንጋት ላይ መካሄድ ተጀምሯል።
ጠቅላላ ጉባኤው “ወሳኙ ወቅት ለተሳሰሩ ችግሮች ለውጥ አምጪ መፍትሔዎች” በሚል መሪ ቃል እንደሚካሄድ በተቋሙ ድረ ገጽ የወጣው መረጃ አመልክቷል።
የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ሌሎች ለዓለም አንገብጋቢ የተባሉ ጉዳዮች በጉባኤው ውይይት እንደሚደረግባቸው ገልጿል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ አባል አገራት የጋራ ፈተናዎችን ለመፍታት እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት መሪዎች በጉባኤው ላይ ንግግር እንደሚያደርጉ የሚጠበቅ ሲሆን ከጉባኤው ጎን ለጎን ትምህርት፣ የዘላቂ ልማት ግቦች አፈጻጸምና የተገፉ ማህበረሰቦች መብት የተመለከቱ ስብሰባዎች እንደሚደረጉም ታውቋል።
ሀንጋሪ የ77ኛውን የመንግሥታቱ ጉባኤ ሊቀመንበርነት ከማልዲቭስ ትናንት በይፋ መረከቧ የሚታወስ ነው።
77ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ በአካልና በበይነ መረብ ጥምረት እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ በአካል የሚካሄድ የመጀመሪያው ጉባኤ ነው ተብሏል።
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW