8ኛው ሀገር አቀፍ የህብረት ስራ ኤግዚቢሽን፣ ባዛር እና ሲፖምዚየም በኦሮሞ ባህል ማዕከል እየተካሄደ ነው

መጋቢት 10/2013 (ዋልታ) – “የህብረት ስራ ግብይት ለዘላቂ ሠላም” በሚል መርህ ቃል 8ኛው ሀገር አቀፍ የህብረት ስራ ኤግዚቢሽን፣ ባዛር እና ሲምፖዚየም ከመጋቢት 9 እስከ 13/2013 ዓ.ም. በኦሮሞ ባህል ማዕከል በመካሄድ ላይ ይገኛል።

66 የህብረት ስራ ማህበራት እና 15 መንግስታዊ ያልሆኑ አምራች ማህበራት በሚሳተፋበት በዚህ ኤግዚቢሽን እና ባዛር በቀጥታ ሽያጭ ከ4000 እስከ 5000 ኩንታል የተለያዩ የግብርና ምርቶች ይሸመትበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከ500 በላይ የተለያዩ የግብርና ምርት አይነቶችም በኤግዚቢሽኑ የሚቀርብ ሲሆን፣ ከ20 ሺህ ኩንታል በላይ የግብይት ትስስር ስምምነት በአምራች  ህብረት ስራ ማህበር እና ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት መካከል እንደሚደረግ ተገልጿል።

አምራች እና ሸማቹን ቀጥታ በማገናኘት  የኑሮን ውድነት ለመቆጣጠር አላማ ተደርጎ በተዘጋጀው  ኤግዚቢሽኑ  ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ በቂ ምርት እንዲያገኙ እንደሚያስችል የፌደራል  ህብረት ስራ ኤጄንሲ ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩሩ ተናግረዋል።

ህብረት ስራ ማህበራት ዘላቂ የሆነ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ለሚሠሩት ስራ ማሳያ ነውም ብለዋል።

የህብረት ስራ ማህበራት ይበልጥ በአመራሩ ከተደገፋ በሀገሪቱ ያለውን ያልተገባ የኑሮ ውድነትን እና የሸቀጦች ዋጋ መናር የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ  ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኤግብሽኑን በይፋ የከፈቱት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር አባይ በአሁኑ ወቅት ተከስቶ ያለው የዋጋ ንረት ሰውን እያማረረ ያለ በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ ይህንን ለመቅረፍ እየሠራ ባለው ስራ ህብረት ስራ ማህበራት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ኤግዚቢሽኒ በህብረት ስራ ማህበራት ቀጥተኛ ትስስርን የሚፈጥር በመሆኑም ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል።

በኤግዚቢሽኑ ከመላው ሀገሪቱ የተወጣጡ ህብረት ስራ ማህበራት ተሳታፊ መሆናቸውም ተጠቁሟል።

(በድልአብ ለማ)