82ኛው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር በዓል በፓናል ውይይት እየተከበረ ነው

ጥር 22/2014 (ዋልታ) የአገው ፈረሰኞች ማኅበር 82ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በፓናል ውይይት እያከበረ ነው።
በ82ኛው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር በዓል ላይ ከሚካሄዱ ሁነቶች አንዱ የፓናል ውይይት ሲሆን በእንጂባራ ዩኒቨርሲቲ እና በብሔረሰብ አስተዳደሩ ትብብር በመዘጋጀት እየተከበረ ይገኛል፡፡
ፈረስ እና የፈረሰኞች ማኅበሩ ታሪካዊ ሂደት እና እድገት፣ ዘርፉን የቱሪዝም ምንጭ ለማድረግ እና የአገው ፈረሰኞች ማኅበርን የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የባሕልና የትምህርት ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ የሚደረገውን እንቅስቀሴ በሚመለከት ውይይት እየተደረገ ነው፡፡
በውይይቱ ምሁራን፣ የማኅበሩ አባላት፣ የአካባቢው ተወላጆች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለሥልጣን ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ተወካዮች መገኘታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡