የመራጮች ምዝገባ ዘግይቶ በተጀመረባቸው ክልሎች መራጮች ምዝገባ መጠናቀቁን ቦርዱ አስታወቀ


ግንቦት 14/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የመራጮች ምዝገባን በአጠቃላይ ያጠናቀቀ ቢሆንም ዘግይተው የጀመሩ ምርጫ ክልሎች ምዝገባ ሲከናወን ቆይቶ በጊዜ ሰሌዳው መሰረት የመራጮች ምዝገባ ትላንትና መጠናቀቁን አስታውቋል።
በዚህም መሰረት የመራጮች ምዝገባ በትላንትና ግንቦት 13 ቀን 2013 የተጠናቀቀባቸው ቦታዎች
• በምእራብ ወለጋ ዞን ( ለቤጊ እና ሰኞ ገበያ ምርጫ ክልል ውጨ)
• በምስራቅ ወለጋ ዞን ( ከአያና እና ገሊላ ምርጫ ክልል ውጪ)
• በቄለም ወለጋ ዞን ( ጊዳም ምርጫ ክልል ውጪ)
• በሆሮ ጉድሩ ዞን ( ከአሊቦ እና ኮምቦልቻ ምርጫ ክልል ውጪ) የሚገኙት 24 የምርጫ ክልሎች ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን ሲከናወን የነበው ምዝገባ እና የአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔር ልዪ ዞን የሚገኙት ዳዋ ጨፌ፣ ጨፋ ሮቢት እና ባቲ ምርጫ ክልሎች በተመሳሳይ ሁኔታ ተጠናቋል።
በዚህም መሰረት በነዚህ ምርጫ ክልሎች የመራጮች መዝገብ ለሚቀጥሉት 10 ቀናት ማለትም እስከ ግንቦት 23 ቀን 2013 ድረስ ለህዝብ ይፋ የሚሆን ሲሆን የመራጮች መዝገባ ቀን ከተጠናቀቀበት ቀን በኋላ ምንም አይነት ምዝገባ ማካሄድ አይቻልም ሲል ቦርዱ አስታውቋል።
ሂደቱም ከዚህ በፊት በቦርዱ የተገለጸ ሲሆን የሚከተሉት ዋና ዋና ሂደቶች የመራጮችን መዝገብ ይፋ ማድረግ ውስጥ ይካተታሉ ብሏል።
– የመራጮችን መዝገብ ለመመልከት የምትቀርብ/የሚቀርብ ሰው የመራጭነት ምዝገባ ካርዷን/ካርዱን እና የማንነት መታወቂያ ካርድ ወይም ማንነቱዋን/ማንነቱን የሚያውቅ ምስክር ማቅረብ አለባት/አለበት::
– የመራጮችን መዝገብ የምትመለከት/የሚመለከት ሰው በመዝገብ ሹሟ/ሹሙ አማካኝነት የምትፈልገው/የሚፈልገውን መረጃ ያለበትን ገጽ /ገፆች/ በዓይን ከማየት ወይም መረጃው ሲነበብላት/ሲነበብለት ከማዳመጥና ማስታወሻ ከመያዝ ውጪ በእጇ/በእጁ መንካት፣ መዝገቡ ላይ መፃፍ፣ ምልክት ማድረግ፣ ወይም ፎቶግራፍ ማንሳት የተከለከለ ነው::
– የመራጮች መዝገብ ህዝብ በግልፅ እንዲያየው ሲደረግ የምርጫ ታዛቢዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም የግል እጩ ወኪሎች እና የምርጫ አስፈፃሚዎች ሊገኙ ይችላሉ፡፡
– እውቅና መታወቂያ ያላቸው የፓለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የእውቅና መታወቂያ ያላቸው የሚዲያ ባለሞያዎች እና ታዛቢዎች ይፋ የሆነውን መዝገብ መመልከትም ሆነ ይፋ የማድረግ ሂደቱን መከታተል ይችላሉ።
– በመራጭነት የተመዘገበች/የተመዘገበ ሰው የመራጮች መዝገብ ለህዝብ ይፋ በሆነበት ጊዜ የግል መረጃዋን/መረጃውን በተመለከተ ስህተት አለ የሚል ቅሬታ ካላት/ካለው እንዲስተካከልላት/እንዲስተካከልለት ለምርጫ ጣቢያው ማመልከት ትችላለች/ይችላል፡፡ ምርጫ አስፈጻሚውም ሰነዶችን በማየት በህጉ መሰረት ማስተካከያ እንደሚያደርግ ከቦርዱ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡