9ኛው የቱሪዝም የእንግዳ ተቀባይነት ሳምንት እየተከበረ ነው

ግንቦት 22/2014 (ዋልታ) በቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚከበረው የቱሪዝም የእንግዳ ተቀባይነት ሳምንት ለዘጠነኛ ጊዜ እየተከበረ ነው።
ሳምንቱ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ የቱሪዝም ሰልጣኞች ክህሎታቸውን የሚያሳዩበት ሳምንት እንደሆነ ተነግሯል።
በ10 ዓመቱ የፍኖተ ብልፅግና ቅድሚያ ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ የቱሪዝም ዘርፍ መሆኑን ያነሱት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈርያት ካሚል ዘርፉን አልምተን እና አጎልብተን እንዴት ተጠቃሚ እንሁን በሚለው ላይ በጥልቀት መመርመር ያሻል ብለዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም በክህሎት የዳበረ የሰው ኃይል ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ ማቅረብ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በሳምንቱ ተማሪዎች በማኅበር ተደራጅተው የፈጠሩትን የሥራ እድል የሚያሳዩ ሲሆኑ የሥራ ትስስር ይካሄዳል።
እንዲሁም ኢንስቲትዩቱ የማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት በቂርቆስ ክ/ከ ለሚገኙ አቅመ ደካማ አረጋውያንን ለ3 ወር የሚቆይ ማዕድ ማጋራት ተግባር ያከናውናሉ።
በዝግጅቱ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈርያት ካሚል ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በዙፋን አምባቸው